አቶ በረከት ስምኦን ሁሉም ብሔረሰብ የራሱን ክልል እያስተዳደረ የሚገኝበት የእኩልነት ስርአት ገንብተናል አሉ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 11/2010) በጎንደር ከተማ በተካሄደው የአማራና የትግራይ ተወላጆች የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት አቶ በረከት ስምኦን ሁሉም ብሔረሰብ የራሱን ክልል እያስተዳደረ የሚገኝበት የእኩልነት ስርአት ገንብተናል ሲሉ ተነገሩ።

በዚሁ መድረክ ኢሳትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ተወግዘዋል።

የአማራ ተወላጆች ልጆቻቸው ለተቃውሞ አደባባይ እንዳይወጡ ይሰበስቡ ዘንድም ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

“አብሮነታችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በጎንደር ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ በረከት ስምኦን በስርአቱ ላይ የተነሱ ተቃውሞዎች አዲስ አበባ ጫፍ መድረሳቸውን በማመን ችግሩ ግን የፌደራል ስርአቱ ያስከተለው ወይንም የውጭ እጅ የፈጠረው ሳይሆን ስልጣን ላይ ባለው አመራር የተከተለ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም መንግስት በቅርቡ ይፋ ካደረገው የደህንነት ፖሊሲ ሰነድ ጋር የሚቃረን ሀሳብ አንጸባርቀዋል።

በሰነዱ የችግሩ ዋና ምንጭ ተብለው የተጠቀሱት የግብጽና የኤርትራ መንግስት መሆናቸው ይታወቃል።

አቶ በረከት በዚሁ መድረክ ሁሉም አካባቢውን ራሱ የሚያስተዳድርበት የፌደራል ስርአት በመዘርጋቱ አንዱ ሌላውን ተጠያቂ ሊያደርግ አይችልም በማለት ይህ የችግር ምንጭ ሊሆን እንደማይችልም ተከራክረዋል።

በክልሎች የውስጥ ጉዳይ ሕወሃት በቀጥታና በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ባለው ሚና ጣልቃ ይገባል በሚል የሚነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ አስተያየት ሳይሰጡ አልፈዋል።

በፌደራል መንግስቱ ውስጥ በመከላከያና ጸጥታ እንዲሁም በኢኮኖሚ ውስጥ ሕወሃት ያለውን ፍጹም የበላይነት በተመልከተም አቶ በረከት በጽሁፋቸው ሳይቃኙት አልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚሁ የአማራና የትግራይ ተወላጆች ጉባኤ ላይ የተገኙና ከትግራይ ክልል የመጡ ወይዘሮ በአማራ ክልል ያለው ችግር እኛም ጋ አለ በማለት ዘርዝረዋል።

የውሃና የመብራት ችግር አለብን ሆኖም እኛ ችግር አለብን ብለን ልጆቻችንን ድንጋይ አናስወረውርም ስለዚህ የአማራ እናቶችም ይህንን አድርጉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ታላቋን ትግራይ ለገነቡ ነው የሚባለውም ውሸት ነው ይህ የኢሳት ወሬ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

እኛ አንድ ነን እነ ታማኝን ለማስደሰት ብለን አማራና ትግራይ መባባል የለብንም ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።