አቶ መኳንንት ካሳሁን በማእከላዊ ድብደባው እንዲቆምለት ፍርድ ቤቱን ጠየቀ

ሚያዝያ ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰማያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ጉዳይ ምክትል ሃላፊ አቶ ብስራት አቢ እና ደቡብ ወሎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ መኳንንት ካሳሁን ከደሴ ከተማ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ከአንድ ወር ከ5 ቀን በኋላ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል። አቶ መኳንንት ካሳሁን ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. አራዳ በሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት “ክቡር ፍርድ ቤት ስለ እግዚአብሔር ድብደባውን አስቁሙልኝ” ሲል ተማጽኖውን አሰምቷል።በችሎቱ አቃቤ ሕግ በበኩሉ “በፈለግነው መንገድ ቃል አልሰጡንም” ማለቱን ተከትሎ ለግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በሁለቱም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው መናገራቸውን እና የአቶ መኳዋንንት ካሳሁን ወላጅ እናት ልጃቸው እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱ ውስጥ በመውደቅ መማጸናቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ተናግረዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማሰርና ማሳደዱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን በባህርዳር 20 አባላት፣ እንዲሁም በጉጂ በገናና ከተማ 7 ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን እና ገዥው ፓርቲ ችግሩ የራሳችን አስተዳደራዊ ችግር ነው ቢልም አሁንም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማሳደዱን መቀጠሉን አቶ የሽዋስ አሰፋ አስታውቀዋል።