አቶ መላኩን ጨምሮ 10 የሚሆኑ የጉምሩክ ሃላፊዎች በቀረበባቸው አንደኛ ክስ እንዲከላከሉ ተወሰነ

ኢሳት (የካቲት 13 ፥ 2009)

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ሃላፊ የነበሩትን አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ 10 ሃላፊዎች በቀረበባቸው አንደኛ ክስ እንዲከላከሉ ተወሰነ።

ፍርድ ቤቱ በቅርቡ በባለስልጣኖቹ ላይ ብይኑን ይሰጣል ተብሎ በተጠየቁበት ወቅት በስፍራው ያለው ድምፅ ችሎቱ ለመሰየም አያስችልም በሚል ቀጠሮውን ለሁለት ጊዜ አራዝሞ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ችሎቱን ወደ ቃሊቲ ሲያዞር አስቀድሞ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት በማለት ቅሬታን ሲያቀቡ የቆዩ ሲሆን፣ ይኸው ችሎት ሰኞ በአንደኛ ክስ ላይ ብይንን እንዲያስተላልፉ የመንግስት መገኛኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎች የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የስራ ሃላፊዎች በሚል ቅርንጫፍ በኩል ከ2003 እስከ 2005 አም ኩባንያዎቹ እቃቸውን ሳያስፈትሹ እንዲያስገቡ አድርገዋል የሚለው ክስ አንደኛው እንደነበር ታውቋል።

በዚሁ ክስ ፍርድ ቤቱ አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ አስር ሃላፊዎችን ጥፋተኛ በማለት የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ወስኗል።

ተከሳሾ በህገወጥ መንገድ ሃብትን ማካበት ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የሚሉና ሌሎች የተናጠል ክሶችም ቀቦባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በሂደት ተጨማሪ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የተከላከሉ ብይን ያስተላለፈው ፍርድ ቤቱ 10ሩ ተከሳሾች መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የተከሳሽ ጠበቆች በደንበኞቻቸው ላይ እየተካሄደ ያለው የክስ ሂደት ከተጠበቀ ጊዜ በላይ ወስዷል በማለት ቅሬታን ሲያርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ የጉምሩክ ባለስልጣናት የስራ ሃላፊዎችና በርካታ ባለሃብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል ተብለው ከአራት አመት በፊት ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም።