አቡነ ጳውሎስ በ76 ዓመታቸው አረፉ

(Aug. 16) የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፤ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጤናቸው እያቆለቆለ መምጣቱ የተገለፀው አቡነ ጳውሎስ፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ንጋት ላይ በባልቻ ሆስፒታል ሕይወታቸው ማለፉንም ቤተክርስቲያኒቱ አረጋግጣለች።
የአቡነ ጳውሎስን ሕልፈት ተከትሎ የቀብር ሥርዓቱን የሚያስፈጽም ኮሚቴ በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት መቋቋሙን  ደጀ ሰላም ዘግቧል።
መኖሪያ ቤታቸውና ቤተ መፃሐፍቱ፤ ጳጳሣት በተገኙበት መታሸጉም ተመልክቷል። አቡነ ጳውሎስ በመንግስት ልዩ ድጋፍ የፓትርያርክነቱን ሥፍራ ማገኘታቸው ይገለጻል።
በአሜሪካኤምባሲ ሚስጥራዊ ሰነድ አማካኝነት የቀድሞ ምክትል ጠ/ሚንስትር ታምራት ላይኔ እንዳረጋገጡት፤ በስደት የሚገኙት ፓትርያርክ አበነ ማርቆሪዮስ ስልጣናቸውን የተነጠቁት በመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሆነም ተመልክቷል።
በመንግስት ልዩ ድጋፍ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ሲነገርባቸው የቆየው ብፁእ አቡነ ጳውሎስ በምላሹም፤ እርሳቸው ለመንግስት የተለየ ድጋፍ በማድረግ የሚወቅሷቸው ተመዘግበዋል።
በስልጣን ዘመናቸው ባልተቋረጠ ተቃውሞ ውስጥ ያለፉት ብፁእ አቡነ ጳውሎስ ከሙስና ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
በቤተክስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ደጀ ሰላም ድረ-ገጽ ህልፈታቸውን ተከትሎ ባቀረበው ዘገባ በአንድ መንግስታዊ ባንክ ቅርንጫፍ ውስጥ በሶስት አካውንት በፓትርያርኩ ዘመዶች ስም 22 ሚሊዮን ብር መቀመጡንም አስፍሮአል።
ከሐምሌ 1984 ኣም ጀምሮ ላለፉት 20 ኣመታት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በመሆን ያገለገሉት አቡነ ጳውሎስ የመጨረሻውን በዓለ ሲመታቸውን ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ሸራተንን ጨምሮ በሶስት ሆቴሎች አክብረዋል።