አቃቢ ህግ ነጻ መረጃ አላገኘሁም በሚል የፈታቸው ባለስልጣናት በድጋሜ ታሰሩ

የካቲት ፫ ( ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በ2007 ዓም በሃመር ወረዳ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ባለመውሰድ ወይም እንዳይወሰድ በማድረግ ለወጣቶቹ በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ ድጋፍ ሰጥታችኋል ተብለው ታስረው የነበሩ የወረዳው ባለስልጣናት መረጃ የለም በሚል አቃቢ ህግ ክስ እንደማይመሰርት ማስታወቁን ተከትሎ ባለስልጣኖቹ ቢፈቱም፣ በድጋሜ እንዲታሰሩ ተደርጓል። ፋይሉን የመረመሩ ዐቃቢያነ ህጎች ደግሞ ከሥራና ደመወዝ ታግደዋል፡፡
የተዘጋው ፋይል እንደገና እንዲከፈት ተደርጎ ከጥር 6 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞው ም/ል አስተዳዳሪና የጸጥታና ፍትህ አርፍ ሃላፊ አቶ እምነት ጋሻው፣ በተቃውሞው ወቅት የዞኑ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ኮ/ል ደመቀ እንዳለ ፣ በተቃውሞው ወቅት የሃመር ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ በርቂ በላይነህ ፣ ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ቡራ ኩሉ ናቸው።
ከሥራና ደመወዝ የታገዱ የዞን ዐቃቤ ህጎች ደግሞ አቶ ዮኃንስ እስተዚያ፣ አቶ አቤነዘር፣ አቶ ነጻዓለም ኪዳነማሪያም፣ አቶ ሚሊዮን፣ አቶ ተመስገን ጋርሾ እና ወ/ሮ ምሥራቅ ናቸው፡፡
በግጭቱ የፌደራልና ልዩ ኃይል ታጣቂዎች ፣ የዞን ፖሊስ አባላትና የሃመር ወረዳ ሲቪል ሠራተኞች መሞታቸው፣ ፖሊስ ጣቢያ መፍረሱ፣ የቱሪስቶች መኪናና የዞኑ ም/አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አወቀ አይኬ መኪና በጥይት መመታት፣ ሃመር ወረዳን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ መዘጋትና ፣ ግጭቱን በሚመለከት የክልሉ ፕ/ት አቶ ደሴ ዳልጌ ሄደው ችግሩን ፈተነዋል ቢሉም፣ እርሳቸው ከተመለሱ በኋላ ወጣቶቹ ተደጋጋሚ የኃይል እርምጃዎች መውሰዳቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ችግሩ እስካሁን እንዳልተፈታ ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጅንካ ለወራት ታስረው ከነበሩት 10 የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች መካከል 6ቱ ሲለቀቁ፣ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ም/ል ሊቀመንበር መምህር አለማየሁ መኮንን፣ የድርጅቱ የዞን ስራ አስፈጻሚ አባል ወጣት ዳዊት ታመነ እንዲሁም አቶ ዘሪሁን ኤቢዞና አቶ አባስ አብዱላሂ በእስር ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
ተፈቺዎች ካልተፈቱት ከእነ አቶ ዓለማዬሁ ጋር እንዳይገናኙ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ማስጠንቀቂያውን ባለመቀበል እየጠየቋቸው እንደሆነ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በእስራት ላይ የሚገኙት የመ/ር ዓለማዬሁ መኮንን የታገደ ደመወዝ በኮማንድ ፖስቱ ደብዳቤ እንዲከፈል ቢታዘዘም በዞኑ ደህንነት ሹም አቶ አልዓዛር አማካኝነት እንዳይከፈል ተደርጓል። በዚህም የተነሳ የታዋቂው ፖለቲከኛ መምህር አለማየሁ ቤተሰቦች ለችግር መዳረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።