አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ

(ኢሳት ዜና– ነሐሴ 3/2009)አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ።
ይህ አሃዝ በፊት ከነበረው በ700 ሺ ጭማሪ አሳይቷል።
የበልግ ዝናብ መዛባት፣የእንስሳት ምግብና ግጦሽ መመናመን እንዲሁም የምርት መቀነስና የውሃ እጥረት በፈጠረው ድርቅ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን ወደ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን አሻቅቧል።
የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ከመንግስታዊ ተቋማት፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ሌሎች የአለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር ባደረገው ጥናት አሳውቋል።
ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 15 2009 የሰብል አብቃይ አካባቢዎችንና የአርብቶ አደር መንደሮችን በማካተት ያደረገው የምግብ ዋስትና ጥናት እንዳመለከተው የእለት ምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በ700 ሺ ያህል አሻቅቧል።
ጥናቱ ከዳሰሳቸው መካከል የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ፣በማሳ ላይ ያለው ሰብል፣የግጦሽና የውሃ አቅርቦት፣የሰውና የእንስሳት ጤና እንዲሁም የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች ስርጭት እንደሚገኝበት በሪፖርቱ አሳውቋል።
በሐምሌ 19 2009 ዋሽንግተን ፖስት የአለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ሳሚር ዋናሚን ጠቅሶ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥራቸው እንደሚጨምር ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ከ450 ሺ በላይ ተረጂዎች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ የተከሰተው ድርቅ የአርብቶ አደሮችን የቀድሞ የአኗኗር ዘይቤ ሊቀይረው እንደሚችል በዘገባው ማመልከቱ ይታወሳል።