አርበኞች ግንቦት7 ተከታታይ ጥቃቶችን መፈጸሙን ተከትሎ ሰሜን ጎንደር ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት አለ

መጋቢት ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት ሰሞኑን በተለያዩ ታጋዮች ስም የተሰነዘሩት ጥቃቶችን ተከትሎ በአካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ በመቀጠሉ ወታደሮች ታጋዮችን ጠቁሙ በማለት ህዝቡን እያስጨነቁት ነው። ቆላ ድባ በመስተዳድሩ ላይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሚሊሺያውና ወታደሮች እየተወዛገቡ ሲሆን፣ ዛሬም ከተማው ተወጥሮ ማወሉን የአካባቢው ምንጮቻችን ገለጸዋል።
በጭልጋ ወረዳ አቦ ከተባለው ቦታ ላይ ትናንት ከምሽቱ 12:30 ላይ ታጋዮች ባደረሱት የደፈጣ ውጊያ አንድ የፀረ ሽምቅ አዛዥ ተገድሎ ሌሎች 3 ወታደሮች ደግሞ በመቁሳለቸው፣ ዛሬ በርካታ የአገዛዙ ወታደሮች ኪንታሆ በሚባል ቦታ ላይ ከታጋዮቹ ጋር እየተዋጉ መሆኑ ታውቋል። የአካባቢው ህዝብ በጡሩምባ እየተጣራ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ባወጀበት እለት ቀይ ዞን ብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚደረሰው ጥቃት እየጨመረ መምጣት ወታደራዊ አዛዦች እርስ በርስ እንዲወዛገቡ አድርጎአቸዋል። ወታደራዊ አዛዦችን የመሾምና የመሻር እንቅሳቀሴ አሁንም ቀጥሎአል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጋዮች ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ እንዳላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የሰሞኑ ጥቃትም በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ የስሜት መነቃቃት መፍጠሩንም እነዚህ ምንጮች ይናገራሉ።