አርበኞች ግንቦት ሰባት በአርባ አምስት ከተሞች የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባና የድጋፍ ማሰባሰብ ዝግጅቶች ማድረጉን አስታወቀ

ኢሳት (የካቲት 6 ፥ 2009)

አርበኞች ግንቦት 7 “እኔ ለነጻነቴ” በሚል መሪ ቃል በአርባ አምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባና የድጋፍ ማሰባሰብ ዝግጅት በስኬት ማጠናቀቁን ገለጹ።

ንቅናቄው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ፌብሯሪ 11 እና 12 ቀን 2017 “እኔ ለነጻነቴ” የሚል ውይይትና የድጋፍ ማሰባሰቢያ ያደረገው በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች፣ በአውሮፓ፣ በካናዳና፣ ደቡብ አፍሪካ መሆኑ ታውቋል።

ከተሞችን በሁለት ቀን በመክፈል በተመሳሳይ ሰዓት በቀጥታ ውይይት በተካሄደው ስብሰባ የድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከትግሉ ስፍራ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፣ በተሰብሳቢዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በስካይፕ ተገኝተው በቀጥታ ምላሽ ሰጥተዋል።

የንቅናቄው ሊ/መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባስተላለፉት መልዕክት “አርበኞች ግንቦት ሰባት የሚታገለው በአገራችን ዕውነተኛ የሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ለማስጀመር እንጂ ስልጣን ለመያዝ አይደለም” በማለት ገልጸዋል።

ዶ/ር ብርሃኑ አያይዘውም ባሳለፍነው አመት የታየው የህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ አርበኞች ግንቦት ሰባት የሚከተለውን ሁለገብ የትግል ስልት ትክክለኛነት ያረጋገጠ ነው” ነው በማለት ገልጸዋል። የነጻነት ትግል ውስጥ ንቅናቄያቸው ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሰብሳቢዎች ለንቅናቄው ሊ/መንበር በትግሉ ሂደት፣ ከሌሎች የለውጥ ሃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት በተለይም በአማራ ክልል ራሳቸውን በጎበዝ አለቃ ካደራጁ ሃይሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ በድርጅታቸው ጥንካሬና የውስጥ አሰራር የተመለከቱ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ “የገጠመን ባላንጣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዳይጀመር ዋነኛ ደንቃራ መሆኑንና መወገድ እንዳለበት በህዝቡ ውስጥ መተማመን በመደረሱ ካለፈው አንድ አመት በፊት ጀምሮ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ አገዛዙ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማውጣት አድርሶታል” በማለት ገልጸዋል። በዚህ ህዝባዊ ዕምቢተኝነት እና የነጻነት ትግል ውስጥ ንቅናቄያቸው ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና የነጻነት ሃይሎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ በተለይም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነት የሚቀበልና ዴሞክራሲያው ስርዓት በአገራችን እንዲገነባ የጸና ዕምነት ካለው ጋር እንደሚሆን አስረድተዋል። በቅርብ ጊዜ የተፈጠረው “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” ለዚህ አባባል እማኝ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ራሳቸውን በጎበዝ አለቆች ካደራጁ ሃይሎች ጋር ተባብረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ፣ ለትግል የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ በመስጠትና በማደራጀት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በቀጣዩም ይህን አስከፊ ስርዓት ለማስወገድ እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት ህዝቡ በፈቀደ አቅሙ ዕገዛውን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በበረሃ ትግል ውስጥ ያሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋይ አርበኞች ለተሰብሳቢውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትብብርና የድጋፍ ጥሪ አስተላልፈዋል።