አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የተላለፈውን ብይን የፍትህ እጦትን የሚያሳይ ድርጊት ነው አለ

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ረቡዕ በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ብይን በኢትዮጵያ ፍትህ እጦትን የሚያሳይ ድርጊት ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

“ጋዜጠኛው ከህዝብ በገሃድ የሚያውቀውን መረጃ ከመግለጽ ውጭ ያደረገው ነገር የለም” ሲሉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የሆኑት ሙቶኒ ዋንዬኬ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኛው ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድም ተቀባይነት የሌለውና ጭካኔ የተሞላበት ነው በማለት ሃላፊው ተናግረዋል።

“መንግስት ትችት የሚቀርብበትን የፍትህ ስርዓት እንደሚያሻሽል በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም እየሆነ ያለው ነገር ግን የፍትህ ሁኔታ እየተጓደለ መምጣት ነው” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት በዮናታን ተስፋዬ ያስተላለፈውን ተመሳሳይ የጥፋተኝነት ብይን ተከትሎ ስጋቱን መገልፁ ይታወሳል።