አምስት የአፍሪካ ሃገራት የአለም ጤና ድርጅት አባልነት ክፍያን ባለመፈጸማቸው ቀጣዩን ዋና ዳይሬክተር በመምረጥ በሚካሄደው ልዩ ጉባዔ ድምፅ አይሰጡም ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 14 ፥ 2009)

አምስት የአፍሪካ ሃገራት የአለም ጤና ድርጅት አባልነት ክፍያን ባለመፈጸማቸው ምክንያት ማክሰኞ ድርጅቱ ቀጣዩን ዋና ዳይሬክተር ለመምረጥ በሚካሄደው ልዩ ጉባዔ ድምፅ እንደማይሰጡ ታወቀ።

ከ180 በላይ የሚሆኑ የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት ማክሰኞ በጀኔቫ በሚያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻ ሶስት እጩ ሆነው ከቀረቡ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አምስት የአፍርካ ሃገራት የድርጅቱን አባላት ክፍያን ባለመፈጸማቸው ምክንያት ድምፅ በመስጠት ሂደት ተሳታፊ እንዳማይሆኑ ስታት ኒውስ የተሰኘ የጤና መጽሄት ከጄኒቭ ዘግቧል። ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ፣ኮሞሮስ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ እና ሶማሊያ የአባልነት ክፍያው ባለፈጸማቸው ምክንያት በምርጫው ድምፅ የማይሰጡ የአፍሪካ ሃገራት መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ከአፍሪካ ሃገራት ቡሩንዲ ከሌሎች ክፍለ አለማት አፍጋኒስታን፣ ኤል ሳልቫዶር፣ እና ቬንዙዌላ ክፍያቸውን እስከማክሰኞ ድረስ መፈጸም ካልቻሉ ድምፅ ላይሰጡ እንደሚችሉ መጽሄቱ በዘግባው አመልክቷል።

የአለም ጤና ድርጅት ወደ 191 የአለም ሃገራት በአባልነት ያየዘ ሲሆን፣ ድርጅቱ በሚያካሄዳቸው ምርጫዎች ክፍያን የማይፈጽሙ ሃገራት መምረጥ እንደማይችሉ መመሪያና ደንብ መሆኑ ታውቋል።

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመጨረሻ ምርጫ ሁለት ሶስተኛ ድምጽ የሚያገኝ ተፎካካሪ ዋና ዳይክተር የመሆን እድል እንዳለው ለመረዳት ተችሏል።

አባል ሃገራት በሚሰጡት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሊገኝ ካልቻለ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጎ አነስተኛ ድምጽ ያገኘ ተፎካካሪ ከውድድሩ ተሰናባች ይሆናል ተብሏል።

ከኢትዮጵያ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከብሪታኒያ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮና የፓኪስታኗ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ለመጨረሻ የቀረቡት ሶስቱ ተፎካካሪዎች ናቸው።

የአለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ተወካይ ተወዳድሮ የማያውቅ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድጋፍ መስጠቱ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነዋሪነታቸው በጀኔቫ ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን ምርጫው በሚካሄደበት ስፍራ የተቃውሞ ሰልፍ እያደረጉ መሆኑን ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ መልኩ ዶ/ር ቴዎድሮስን የሚደግፉ ሰዎች ተመሳሳይ ሰልፍ ማክሰኞ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

አዲሱ የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ከተሰናባቿ ቻይናዊ ሃላፊነት ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።