አሜሪካ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የአለም ሙቀትን ለመቀነስ ከተደረሰው ስምምነት መውጣቷን ይፋ አደረገች

ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2009)

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ከሁለት አመት በፊት በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የአለም ሙቀትን ለመቀነስ ከተደረሰው ስምምነት መውጣቷን ይፋ አደረጉ።

የፓሪስ ስምምነት በመባል የሚታወቀው ይኸው አለም አቀፍ የአካባቢ ስምምነት በ187 ሃገራት መካከል ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ ዕርምጃውም የአለም ሙቀትን በሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ታውቋል። ይሁንና በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የፓሪሱን ስምምነት ውድቅ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ስምምነቱ በድጋሚ ለድርድር መቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል።  

ከሁለት አመት በፊት የአለም ሙቀትን ለመቀነስ በአለም ሃገራት መካከል ተፈርሞ የነበረው ስምምነት የአሜሪካንን ጥቅም እጅጉኑ የሚጎዳ ነው ሲሉ ፕሬዚደንት ትራምፕ የሃገራቸውን ከስምምነት መሰናበት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።

ይኸው የፓሪስ ስምምነት አሜሪካን ከአጠቃላይ አመታዊ ምርት 3 ትሪሊየን ዶላር ሊያሳጣት እንደሚችልና 6.5 ሚሊዮን ሰዎችም በስምምነቱ ተግባራዊነት ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ፕሬዚደንቱ ገልጸዋል።

ለአለም ሙቀት መጨመር እና ለአካባቢ መበከል ዋነኛ ተጠያቂ የምትደረገው ቻይና እና ህንድ በስምምነቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል ሲሉም የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አክለው ተናግረዋል።

ቻይናን ጨምሮ ምዕራባውያን ሃገራት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ከስምምነቱ መውጣት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመግለጽ ላይ ሲሆኑ የአካባቢው ተቆርቋሪዎችም በአሜሪካ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ይገኛል። በአለማችን ካሉ ሃገራት መካከል በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሶሪያ እና ኒካራጓ ብቻ የፓሪሱን ስምምነት እንዳልፈረሙ ቢቢሲ ዘግቧል።

“ከእንግዲህ በኋላ ማንም መሪና ሃገር እንዲስቅብን አንፈልግም” ሲሉ ፕሬዚደንት ትራምፕ ሃገራቸው በስምምነቱ ደስተኛ አለመሆኗን አክለው ገልጸዋል።

አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በበኩላቸው አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን ማግለሏ በፓሪስ የተደረሰው የአለም ሃገራት ወደ ተግባር እንዳይለወጥ እቅፋት እንደሚሆን አስታውቀዋል። አሜሪካ ወደ ስምምነቱ መቼ እንደምትመለስ የሰጠችው የጊዜ ገደብ ባይኖርም፣ ባለሙያዎችና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አራት አመት ሊፈጅ እንደሚችል ተናግረዋል።

የፓሪሱ ስምምነት ፈርመው የነበረ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በአዲሱ ፕሬዚደንት ውሳኔ ቅሬታ እንደተሰማቸው በመግለጽ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን አጥብቀው ኮንነዋል።

የፕሬዚደንቱ ውሳኔ በምክር ቤት አባላት ዘንድ ሳይቀር ልዩነትን የፈጠረ ሲሆን፣ የድንጋይ ከሰል አምራችና ተጠቃሚ ኩባንያዎች ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ፈረንሳይ፣ ጀርመንናክ፣ ጣሊያን በጋራ ባወጡት መግለጫ የፓሪሱ ስምምነት ዳግም ድርድር እንዳማይካሄድበት ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አሜሪካ ከፓሪሱ ስምምነት ራሷን ማግለሏ በአፍሪካ ሃገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የአካባቢ መብት ተሟጋቾች አርብ አስታውቀዋል።

ሃገሪቱ ከስምምነት መሰናበቷ ለአህጉሪቱ የምትሰጠው ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ አመታዊ ድጋፍ እንዲቋረጥ እንደሚያደርገው የደቡብ አፍሪካው የወርልድ ዋይልድ ላይፍ ፈንድ (World Wildlife Fund) ሃላፊ ሳሊም ፋኪር ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። በርካታ ሃገራት ድርጅቶች የአሜሪካንን ዕርምጃ በመኮንነን መግለጫን እያወጡ ይገኛል።