አማራና ቅማንትን በጎጥ ለመከፋፈል የተጠነሰሰው ሴራ በአስቸኳይ እንዲቆም የጎንደር ህብረት አስጠነቀቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 25/2009)አማራና ቅማንትን በጎጥ ለመከፋፈል በትግራይ ሕወሃት ነጻ አውጭዎች የተጠነሰሰው ሴራ በአስቸኳይ እንዲቆም የጎንደር ህብረት አስጠነቀቀ።

ሕብረቱ ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የጎንደር ሕዝብ አማራና ቅማንትን ለመከፋፈል መስከረም 7/2010 የታቀደውን ሕዝበ ውሳኔ በማክሸፍ መሬቱ ለትግራይ ከመተላለፉ በፊት አካባቢውን እንዲያድን ጥሪ አቅርቧል።

ሕወሃት በራሱ ክልል የሚገኙትን የኩናማ፣የኢሮብና የአገው እንዲሁም የአፋር ጎሳዎችን ሳይከፋፍልና የሕዝበ ውሳኔ መብት ይሰጣቸው ሳይል የአማራና ቅማንትን ሕዝብ በመብት ስም መከፋፈሉ የትግራይን ግዛት ለማስፋፋት ካለው ሕልም ጋር የተገናኘ መሆኑን የጎንደር ሕብረት መግለጫ አትቷል።

ዳር ድንበርን ቆርሶ፣ሀገር አፍርሶ የትግራይን ግዛት ለማስፋፋት የሚደረገው ሴራ በሕዝባችን ጥበብ ይቀለበሳል በሚል የጎንደር ሕብረት ወቅታዊ መግለጫ አውጥቷል።

መነሻው ደግሞ መስከረም 7/2010 አማራና ቅማንትን ለመከፋፈል በ12 ቀበሌዎች ተዋህደው በሚኖረው ሕዝብ መካከል ድምጽ እንዲሰጥ በምርጫ ቦርድ መወሰኑ ነው።

የጎንደር ሕብረት መግለጫ እንደሚለው አማራና ቅማንትን ለመለያየት የተፈለገው የአካባቢውን ለም መሬት በኋላ ላይ ለትግራይ ክልል ለማድረግና የሕወሃትን የግዛት መስፋፋት ህልም እውን ለማድረግ ነው።

ይህ ባይሆን ኖሮ ለዘመናት በትግራይ ክልል የሚኖሩ የኢሮብ፣የኩናማ፣የአገውና የአፋር ብሔሮች እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይደርግ ነበር ሲል መግለጫው ይጠይቃል።የጎንደር ሕብረት ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ንጋቱ ስለሁኔታው ይናግራሉ።

የወልቃይት ጠገዴ፣የወሎ ራያን ለም መሬቶች ሕወሃት በስርቆት የወሰደውም ራስን በማስተዳደርና በቋንቋ ሰበብ መሆኑን የጎንደር ሕብረት አስታውሷል።

በቅርቡ እንኳን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቴሌቪዥን የትግራይን የመስፋፋት ህልም ማሳየቱና በኋላም ላይ ይቅርታ መጠየቁ አንድ ማስረጃ ነው ብሏል።
የአማራና የቅማንትን ሕዝብ ከፋፍሎ በሚፈጠረው ግዛትና አካባቢ የሕወሃት ተላላኪዎች የወታደራዊ፣ የመረጃና የልዩ ኮማንዶ አባላትን ማሰልጠን መጀመሩንም የጎንደር ሕብረት አጋልጧል።

በዚሁም የትግራይ ካድሬዎችና መኮንኖች የሚሳተፉበት ክፍለ ጦር እንደሚቋቋምና በሚፈጠረው አዲስ የቅማንት ግዛት እንደሚሰማራም ለማወቅ ተችሏል ብሏል መግለጫው።

ይህም በመሆኑ መላው የጎንደር ሕዝብና ኢትዮጵያውያን የአማራና ቅማንት ሕዝብን የመከፋፈል ስራ ለማክሸፍ በጋራ እንዲቆም ጠይቋል።

የሱዳን አንድ ክፍለ ጦር በቋራ ሽንፋ በወረራ ላለፉት ሁለት አመታት የያዘውን የኢትዮጵያ ምድርም በአስቸኳይ እንዲለቅ የጎንደር ሕብረት መግለጫ አሳስቧል።

በወልቃይት ጠገዴ፣ቃብቲያ ሁመራ እንዲሁም ጠለምትና ራያ በጉልበት በትግራይ ክልል በመወሰዳቸው እነዚሁም የጎንደር ግዛቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠይቋል።

ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ፣ኣቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፥ዶክተር መረራ፥ ጉዲናና አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱም ጥሪ ቀርቧል።