አመታዊው የምስጋና ቀን ተከብረ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 14/2010)አመታዊው የምስጋና ቀን/ታንክስ ጊቪንግ/ዛሬ በአሜሪካኖች ዘንድ ተከብሮ ዋለ።

በአሜሪካ የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ሁኔታና አቅም በፈቀደ መጠን በአሉን ያከብራሉ።

በአሜሪካውያኑ ዘንድ በያመቱ በህዳር ወር 4ኛው ሀሙስ ላይ የሚከበረው የምስጋና ቀን/Thanksgiving/ ምስጋና የሚሰጥበትና ቤተሰብና ጓደኛ ሰብሰብ ብሎ የሚያከብረው ቀን ነው።

በአሜሪካና ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሁኔታው እንደፈቀደላቸው ሰብሰብ ብለው ያከብሩታል።

በአሉ በካናዳ ባለፈው ወር ተከብሯል።

በአሉ በካሪቢያን ደሴቶችና በአፍሪካም በላይቤሪያ እንደሚከበር ይታወቃል።

የምስጋና ቀን ታሪካዊ አመጣጥ ላይ ጥርት ያለ ስምምነት ባይኖርም በአብዛኛው ግን ከሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ጋር ተያይዞ መከበር የተጀመረ በአል እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮም ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ በመጡ ስደተኞች እንደተጀመረም የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ።

ከእንግሊዞችም በፊት ቀድመው በአሜሪካ የነበሩ ኢንዲያን ወይም ኔቲቭ አሜሪካን ተብለው የሚጠሩት በአሉን አይቀበሉም።

ለእነሱ ይህ በአል ማለት በመጤ ነጮች መጨፍጨፋቸውን የሚያስታውሳቸው ነው።

ለረጅም ሰአታት ስትጠበስ የምትውለዋን አንገተ መላጣዋን ሙሉ ዶሮ ተርኪ ይሏታል በዚህ በአሜሪካ።

ከሌሎች ማጣፈጫዎችና ተጨማሪ ምግቦች ጋር በትልቅ ጠረጴዛ ቀርቦ ቤተሰቦች ዙሪያውን ተሰብሰበው ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ያንን እየተመገቡ ሲጨዋወቱ ይውላሉ።

እያንዳንዱም ሰው ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በምን ምክንያት አምላኩን እንደሚያመሰግንም ይናገራል።

ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታ ያለው ይህ አውደ አመት በሌሎችም መንገዶች ሲከበር ይውላል።

በየከተሞቹ የምስጋና ቀን ሰልፍ/Thanksgiving parade/ ሲደረግ በኒዮርክ የሚደረገው አመታዊው ሜሰስ ታንክስ ጊቪንግ ሰልፍ በጣም ትልቁ ነው።

በማግስቱ ታዲያ ብላክ ፍራይደይ ነው።ሱቆች እቃዎቻቸውን በርካሽ የሚሸጡበት ቀን በመሆኑ ተጨናንቀው ይውላሉ።

አንዳንድ ደንበኞች የሚፈልጉት ዕቃ እንዳያመልጣቸው በሌሊት ሄደው ሰልፍ ይይዛሉ።

በኋይት ሃውስ በልማድ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንቱ ሁለት እድለኛ የሆኑ ተርኪዎችን ምህረት ያደርጉላቸውል።

በዚህም መሰረት ባለፈው ማክሰኞ ድራምስቲክና ዊሽቦን በሚል መጠሪያ ለሚታወቁት ሁለት ተርኪዎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምህረት አድርገውላቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ከነ ቤተሰባቸው ለመላው አሜሪካውያን መልካም በአል ተመኝተዋል።

የዛሬ ወር ገደማ ደግሞ ገና ይከበራል።ሁለቱ በአላት አሜሪካውያን ከስራና ከጉዞ ታቅበው ቤት የሚውሉባቸው ሁለት ቀናት ናቸው።

የዛሬው የምስጋና ቀን አሜሪካኖች እስከ ገና ድረስ ለአንድ ወር የሚቆየውን የአውደ አመት ስሜት መፍጠር የሚጀምሩበት ቀንም ነው።