አልሸባብ አልቃይዳን በይፋ መቀላቀሉ ተገለፀ

የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአልቃይዳዉ መሪ በእስልምና ተከታዮች ፎረም ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰዉ አልሸባብ በፀረ ፅዮናዊነት የሚደረገዉን የጅሃድ ዘመቻ በመቀላቀል የአልቃይዳ አባል መሆኑ እሳቸዉንና እምነት ያላቸዉን እንደሚያስደስት፤ በተቃራኒዉ እምነት የሌላቸዉን ሊያስደነግጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

የአልቃይዳዉ መሪ በተጨማሪ በሶማሊያ የሚገኙ የእስልምና ተከታዮች ዉሸትን የሚሰብኩትንና ንፁህ በሆነዉ የእስላም ምድር ላይ ይህን መአት ያመጡትን ደካማ የሶማሊያ መሪዎች እንዳይቀበሏቸዉ ጥሪ አድርገዋል።

አምና በፓኪስታን በዩናይትድ ስቴትስ መንግሰት በተደረገዉ ጥቃት ኦሳማ ቢን ላዲን ከተገደሉ በሁዋላ የአልቃይዳዉ መሪ ለሆኑት አል ዘዋ-ሂሪ ያላቸዉን ታማኝነት በመግለፅ የአልሸባቡ መሪ ሺክ አቡ ዙቤር የተናገሩት የድምፅ ቅጂ በቪዲዮ መልእክቱ ዉስጥ መካተቱን በተጨማሪ ለማወቅ ተችሏል።   

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሞቃዲሾ ሙና ሆቴል ትናንት ሃሙስ ተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ፈንጂ  10 ሰዎች ን መግደሉን ተከትሎ በአፍሪቃ ህብረት ልዩ ኮሚሽን የሶማሊያ አምባሳደር ቡባካር ጉሱ ዲያራ አልሸባብን መወንጀላቸዉ ታዉቋል።