አልሸባብ ለኢትዮጵያ ሰራዊት ሲሰልል ነበር ባለው አንድ የሃገሪቱ ተወላጅ ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን ገለጸ

ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2009))

የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ በሃገሪቱ ተሰማርቶ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲሰልል ነበር ባለው አንድ የሃገሪቱ ተወላጅ ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙ ተገለጸ።

ሰይድ መሃመድ አሊ የተባለው የሶማሊያ ተወላጅ የተለያዩ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ ወታደሮች በማቀበል አልሸባብ የጥቃት ኢላማ እንዲሆን ማድረጉን ታጣቂ ሃይሉ ማስታወቁን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በርካታ ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የተካሄደው የሞት ቅጣት በማዕከላዊ የጁባ ግዛት ስር በምትገኘው የቡአሌ ከተማ መሆኑን የአልሸባብ ራዲዮ ጣቢያ የሆነውን አንዳሉንስ ዋቢ በማድረግ አሶሼይትድ ፕሬስ አስነብቧል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ተሰማርቶ ከሚገኘው የሰላም አስከባሪ የልዑካን ቡድን በተናጠል በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች በማሰማራት በታጣቂ ሃይሉ ላይ ጥቃት ስትፈጽም መቆየቷ ይታወቃል።

ይሁንና ከወራት በፊት በርካታ ወታደሮች ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለቀው የወጡ ሲሆን፣ አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ እነዚሁኑ አካባቢዎች ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ሲገለጽ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወታደሮቹ ለቀው እንዲወጡ የተደረገው ለስልታዊ ዕርምጃ መሆኑን በመግለጽ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለሶማሊያ መንግስት የሚጠበቀውን ድጋፍ አለማድረጉም ተጨማሪ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ማስታወቁ ይታወሳል።

የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪ ቡድኑ ሲሰጥ የነበረውን ድጋፍ ለመቀነስ መወሰኑን ተከትሎ ቡሩንዲና ዩጋንዳ በሶማሊያ ያሰማሩትን ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት መወሰናቸው አይዘነጋም።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ማላዊ፣ ቡሩንዲና፣ ጅቡቲ የተውጣጡ ከ20 በላይ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሃገሪቱ ተሰማርተው ቢገኙም አልሸባብ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ ይገኛል። በሞቃዲሾ እና ሌሎች ከተሞችም የሚፈጽማቸው ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመሄድ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።