አልሸባብ ሂራን በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ላይ ጥቃት አደረሰ

ግንቦት ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር አሜሶም ስር በሶማሊያ በተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ላይ አሸባሪው አልሸባብ ጥቃት ፈጸመ። ረቡእ እለት በሂራን ግዛት በሃላጋን ከተማ በሁለቱም መሃከል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። እስካሁን በግጭቱ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ አልተቻለም።
አልሸባብ በራሱ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ወታደራዊ ቤዝ ላይ ባደረሰው ጥቃት በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደሉን እና የተወሰነውን የከተማዋን ክፍል ከአሜሶን እጅ መቆጣጠሩን አስታውቋል።
የሶማሊያ መንግስት እና የአሜሶም ባለስልጣናት በበኩላቸው የሃላጋንን ጥቃት አስመልክቶ እስካሁን ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጡም። አልሸባብ ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ከተማዋን ጥሎ ማፈግፈጉን በሶማሊያ ጦር እና በሰላም አስከባሪው አሜሶን ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አጠናክሮ መቀጠሉን ጋሮ ኦንላይን አክሎ ዘግቧል።