አለማቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን በፍጥነት አለመዘርጋቱ ጭንቀት ፈጥሯል

የካቲት ፮ ( ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ወር መጀመሪያ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ጭምር በአባልነት የሚገኙበት የድርቅ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኮምቴ ለቀጣዩ አንድ ዓመት ለድርቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ይፋ ቢያደርግም የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ምላሽ እጅግ የተቀዛቀዘ መሆኑ አገዛዙን አሳስቦታል።
ከብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት የመኽር ዝናብ ማለትም በያዝነው ዓመት ከጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት እስከ ታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ካለመዝነቡ ጋር ተያይዞ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ለአስቸኳይ የዕለት ምግብ ዕርዳታ ጠባቂነት ተጋልጠዋል፡፡ ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት 948 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ባለፈው ወር የመጀመሪያ ሳምንት በይፋ የድረሱልን ጥሪውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አቅርቧል፡፡ ይህም ሆኖ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከካቻምና እና አምና በባሰ መልኩ ምላሹ እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑ ገዢውን ፓርቲ አስደንግጦታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገው 948 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም 598 ሚሊየን ዶላር የሚስፈልገው ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ግዥ ነው፡፡ ቀሪው ገንዘብ ድርቁን ተከትለው ለሚከሰቱ ለጤና፣ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለትምህርት፣ ለእርሻና ተፈጥሮ ሐብት እንክብካቤ፣ ለመጠለያና ቁሳቀስ ግዥ፣ ለሴቶችና ህጻናት ችግሮች መፍቻ የሚውል ነው፡፡
አገዛዙ አንዳንድፕሮጀክቶችን በማዘግየት ከእጅ ወደአፍ ከሆነው የውጪ ምንዛሪ ገቢው ላይ እስካሁን 47 ሚሊየን ዶላር ገደማ ለድርቅ ለመመደብ የተገደደ ሲሆን፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ አሁን በሚታየው መልኩ ተቀዛቅዞ የሚቀጥል ከሆነ አገዛዙ በአንድ ወር ብቻ እስከ 80 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ እንዲያወጣ ይገደዳል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ይገመታል።
በአሁኑ ወቅት በአንደኛ ደረጃ የተጠቃው የሶማሌ ክልል ሲሆን፣ ክልሉ ካሉት 11 ዞኖች 9 ያህሉ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሶማሊ ክልል በቅርቡ ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች ማቋቋሚያ ይሆን ዘንድ 11 ሚሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መለገሱ ይታወቃል።