ንግድ ባንክ የወጭ ገንዘብ አገልግሎት መስጠት ማቋረጡን ተከትሎ ከደንበኞቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባ

ሰኔ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዘጋቢያችን እንደገለጠው ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሁሉም ቅርንጫፎች የወጭ ገንዘብ አገልግሎት መስጠቱን አቋርጧል። በመሀል መርካቶ አባኮራን ቅርንጫፍ በባንክ ሰራተኞችና በደንበኞች መካከል ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ አንድ የባንኩ ሀላፊ ችግሩ የሰራተኞች አለመሆኑንና የቴሌ ሰርቨር የፈጠረው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ከግንቦት 1 ጀምሮ በቴሌ ኔት ወርክ መጠቀም በመጀመሩ ደንበኞች በየትኛውም ቅርንጫፍ መገልገል ይችሉ ነበር በማለት አንድ የባንክ ሰራተኛ ገልጠው፣ ነገር ግን መንግሰት ሁሉንም ነገር ፖለቲካዊ ለማድረግ ስለሚፈልግ ያለአቅማችንና በቂ ዝግጅት ሳናደርግ የገባንበት አሰራር ብዙ ጊዜ እየተቋረጠ ከደንበኞቻችን ጋር እያነታረከን ይገኛል ብለዋል።

ዘጋቢያቸን የተለያ  የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን በወጭ ሂሳብ አገልግሎት መስተጓጎል የተነሳ ተገልጋዮች ከአንድ ቅርንጫፍ ወደ ሌላ ቀርንጫፍ ሲመላለሱ ያለምንም አገልግሎት ወደ መጡበት መመለሳቸውን እና የስራውን መጀመር በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጠዋል።

አንድ የፒያሳ ቅርንጫፍ ሀላፊ እንደተናገሩት ዋናው ባንክ ከቴሌ ሀላፊዎች ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እየጣረ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ደንበኞች እስከ 3 ሺ ብር ብቻ ማውጣት እንደሚችሉና የሂሳብ ስህተት ከተገኘም የባንኩ ኪሳራ እንደሚሆን ተናግረዋል። ከ3 ሺ ብር በላይ ገንዘብ ለማውጣት መወሰን ይከብዳል የሚሉት ሀላፊው ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ የሰርቨሩ መቋረጥ ደንበኞች ያደረጉትን የገንዘብ ልውውጥ ስለማያሳይ በባንክ ደብተር ብቻ ለመወሰን ይከብዳል ብለዋል።  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በማብዛት እና ዲጂታል በማድረግ ለትራንስፎርሜሽኑ እቅድ የበኩልን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ከአንድ ወር በፊት ወደ አዲሱ አሰራር መግባቱን ያወሱት ባለስልጣኑ ፣ በመጨረሻ ግን ” አልቻንበትም” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የባንኩ ደንበኞች እስከ 3 ሺ ብር ድረስ ማውጣት እንደሚችሉና በመሀል ለሚፈጠረው ችግር ባንኩ ኪሳራውን እንደሚሸፍን መነገሩ አንዳንዶች ገንዘብ በፍጥነት እንዲያወጡ ሳያበረታታቸው እንደማይቀር ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።

በቴሌ የሚታየው የሰርቨር መቆራረጥ ምክንያቱ ከውጭ የሚተላለፉትን የመገናኛ ብዙሀን ለማፈን ከሚደረገው ጥረት ጋር እንደሚያያዝ በቴሌ ውስጥ አገልግለው በቅርቡ ከስራ የተሰናበቱ አንድ ሀላፊ ተናግረዋል። በመላ አገሪቱ የሚታየው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከሙን የገለጡት ሀላፊው፣ ከውጭ የሚተላለፉትን ጣቢያዎች ለማፈን ሲባል በአገር ውስጥ ያለው ህዝብ ፍዳውን እየከፈለ ነው ይላሉ። ማንኛውም የኢሳትን ዝግጅቶች በፌስ ቡክ፣ በዩቲዩብ እና በሌሎችም መንገዶች ፈጽሞ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ሀላፊው ገልጠዋል።

በፈረንሳዮች እገዛ በቀድሞ የህወሀት ጀኔራሎች የሚመራው ቴሌ የውጭ የመገናኛ ብዙሀንን ለማፈን በሚያደርገው ሙከራ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይገልጣሉ።

ባለፈው ሳምንት ለዝርዝር እይታ የተመራው አዲሱ የቴሌ ህግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን መጠቀም በወንጀል እንደሚያስቀጣ ጠቅሷል። በአዲሱ ህግ መሰረት ስካይፕ እና ቫይበርን የመሳሰሉ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እስከ 15 አመት እስራትና 300 ሺ ብር ቅጣት ያስቀጣል።

መንግስት በኢንተርኔት የተነሳ የአገሪቱ ደህንነትና ጸጥታ አደጋ ላይ ወድቋል በማለት ነው አዲስ ህግ ለማውጣት የተገደደው። በአገር ቤት በእንግሊዝኛ የሚታተመው ፎርቹን ጋዜጣ በዚህ ሳምንት ርእሰ አንቀጹ አዲሱን የቴሌኮሚኒኬሽን ህግ  በጽኑ ተቃውሟል። ጋዜጣው ህጉ የግለሰብን ነጻነት የሚገፍ፣ ፈጠራን የሚገድል፣ ህዝቡ እንዳያስብ፣ እንዳይመራመርና እንዳይሻሻል የሚያደርግ ህግ ነው በማለት ኮንኖታል። ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር የሚፈልገው ገዢው ፓርቲ፣ የአገሪቱ ደህንነትና ጸጥታ አደጋ ላይ ወደቀ በማለት ኢንተርኔትን ለማፈን ቢነሳም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአፈናው ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል አገሪቱን ደህንነት ይበልጥ አደጋ ላይ ይጥላል ሲል አስጠንቅቋል።

ፎርቹን በርእሰ አንጸቁ ገዢው ፓርቲ ከዚህ በፊት ሳተላይት ቴሌቪዥንና ማስተር ካርድን መጠቀም በወንጀል እንደሚያስቀጣ ደንግጎ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል ካለ በሁዋላ፣ ኢንተርኔትን ለማፈን የሚደረገው ጥረትም አይሳካም ብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide