ኒኮላስ ዲ ክርስቶፍ መለስ ዜናዊ በወሰደው የጭካኔ እርምጃ የዓለምን የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት የበለጠ ከመሳብ ውጭ ጸጥ ሊያሰኝ አይችልም አለ

ጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ታዋቂው የዘ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አምደኛ የሆነው ኒኮላስ ዲ ክርስቶፍ መለስ ዜናዊ በስዊድን፣ አሜሪካና ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ በወሰደው የጭካኔ እርምጃ የአለምን የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት የበለጠ ከመሳብ ውጭ ጸጥ ሊያሰኝ አይችልም ብሎአል።

ኒኮላስ ዲ ክርስቶፍ እንደጻፈው አስቀያሚ በሆነው የኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ ቅማል፣ ቁንጫና አይጥ በሞላበት እስር ቤት ውስጥ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብየ እና ጋዜጠኛ ጆን ፔርሰን ታስረዋል።

እስር ቤቱ የጸጥታ መደፍረስ የሚታይበት፣ በበሽታ የተበከለ፣ እና እስረኞቹ  በየጊዜው የሚደባደቡበት ቦታ መሆኑን የሽብየን ባለቤት ዋቢ በማድረግ ኒኮላስ ገልጧል።

ጋዜጠኞቹ ምን ጥፋት አጠፉ? ጥፋታቸው ጀግንነታቸው ብቻ ነው የሚለው ኒኮላስ ፣ ወደ ኦጋዴን የተጓዙት በአካባቢው ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጋለጥ ነው ብሎአል።

መለስ ጋዜጠኞችን ሲያስር ዋና ምክንያቱ ለሌሎች የአለም ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው ዝር ትሉና አሳያችሁዋለሁ ለማለት ነው የሚለው ኒኮላስ፣ ትክክለኛው መልስ የመለስን እያሽቆለቆለ የሄደ የሰብአዊ መብት ረገጣ በጥንቃቄ መመርመር ነው ይላል።

የሚያሳዝነው ለመለስ መንግስት ጭቆና ዋሽንግተን እና ሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ድጋፍ እየሰጡት ነው።

የስዊድን ጋዜጠኞች ምናልባትም በአለማቀፍ ግፊት የተነሳ ሊለቀቁ ይችላሉ፣ ነገር ግን ቁጥር ስፍር የሌላቸው የኢትዮጵያ እስረኞች ከእስር፣ ስቃይና አስገድዶ መደፈር እረፍት አያገኙም ብሎአል።

“እኔ እና መለስ በዳቮስ ስዊዘርላንድ ለአለም የኢኮኖሚ ፎረም ተገናኝተን ነበር። ላለፉት ጥቂት ቀናት ከእርሱ ጋር ለመገናኘት እና እየፈጸመ ስላለው ጭቆና ለማነጋገር ስሞክር ቆይቻለሁ። ነገር ግን እኔን ለማየት  አልፈለገም” ይላል ኒኮላስ።

.መለስ ድህነትን በመዋጋት በኩል ጥሩ ስራ ሰርቷል፤ በስሩ በጣም ጥሩ የሆኑ ሰዎች አሉት፣ በጤናውና በእርሻው በኩል ኢኮኖሚው እያደገ ነው፣ ኢትዮጵያም ብዙ ለጋ  አገሮች በአገሩዋ ይገኛሉ፤ አሜሪካም ከመለስ መንግስት ጋር ጥሩ የሆነ የስለላ እና የወታደራዊ ግንኙት አላት የሚለው ኒኮላስ፣ ይሁን በ1997 ዓም 200 ሰዎች በጸጥታ ሀይሎች ከተገደሉና ከ 30 ሺ በላይ የሚሆኑት ከታሰሩ በሁዋላ መለስ ጭቆናውን ቆጥሎበታል።

መለስ የእርዳታ እህልን ለፖለቲካ ድጋፍ መግዢያ እያዋለው መሆኑን፣ መላው ህዝብ እርሱን ካልደገፈ በረሀብ እንደሚቀጣው ጽፎአል።

የመለስ መንግስት በጥቂት የትግራይ ተወላጆች እንደሚሽከረከርም ጋዜጠኛው ጠቅሶአል።

ኒኮላስ በመጨረሻም ለአቶ መለስ በላከው መልክት ” ዳቮስ ውስጥ እኔን ቢሸሹኝም በጋዜጠኞች ላይ የፈጸሙት ግፍ ግን የአለም ሚዲያ ከአንተ  እንዳይሸሹ ያደርጋል።” ብሎአል።