ቻይና በጅቡቲ ወደብ የጦር ሰፈሯን ገነባች 

 

(ኢሳት ሐምሌ 5/2009)የቻይና የባህር ሀይል የአፍሪካ ትንሿ ሀገር በመባል በምትታወቀው ጅቡቲ የጦር ሰፈሩን ከመመስርቱ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 በአካባቢው ጉብኝት አድርጎ ነበር።

የቻይና ጦር ሰራዊትን የያዘችው መርከብ በአካባቢው ጉብኝት ስታደርግም ቤጂንግ ከሀገር ውጭ ለምትገነባው የጦር ሰፈር መሰረት የጣለችበት ወቅት እንደነበር ነው ዥንዋ በዘገባው ያመለከተው።

የጦር ሰፈሯን በጀቡቲ ያደረገችው ቻይና የባህር ሃይሏ ተልእኮ በዋናነት የሰላም ማስከበርንና የሰብአዊ እርዳታን በአፍሪካና በምእራብ ኢሲያ ሀገራት ላይ እንዲያዳርስ ማድረግ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ወታደራዊ ትብብር ፣   የባህር ላይ ልምምድና የአደጋ ጊዜ ስራዎችን ማከናወን ሌላኛው የባህር ሃይሉ ተጋባር ነው።

ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን የንግድና የኢቨንስትመንት ግንኙነት ማዳበር እየዘመነ የመጣውን ወታደራዊ ሃይሏን የበለጠ ማጠናከር የሚለውንም አጀንዳ ነድፋለች።

እንደ ዥንዋ ዘገባ የጦር ሰፈሩ ግንባታ ባለፈው አመት ሲጀመርም ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን የሁለትዮሸ ግንኙነት ለማጠናክር ከስምምነት ደርሰው ነበር።

ቻይና በአካባቢው የጦር ሰፈሯን ማድረጓ ሀገሪቱ በቀጠናው ያላትን ተሰሚነት ያጠናክረዋል ብሏል ዘገባው።

ሀገሪቱ በአካባቢው የጦር ሰፈሯን ታደራጅ እንጂ ስለ ምታሰማራው የመርከብም ሆነ የጦር ሰራዊት ቁጠር የወጣ መረጃ የለም።የጦር ሰፈሩ ስራዉን መቼ ይጀምራል ለሚለውም የተሰጠ ምላሸ የለም ብሏል ዥንዋ በዘገባው።

እንደ ሪፖርቱ ቻይና በቀጠናው መዋእለ ንዋይዋን በማፍሰስና በተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሰው ሃይሏን በማሰማራት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛልች።

ከቻይና ሌላ በአካባቢው አሜሪካ፣ጃፓንና ፈረንሳይ የጦር ሰፈራቸውን መስርተዋል።