ትጥቅ ለማስፈታት በሚል በተለያዩ የጎንደር አካባቢዎች የአጋዚ ጦር መስፈሩ ተነገረ

ሰኔ 21 ፥ 2009

የጎንደርን ህዝብ ትጥቅ ለማስፈታት በሚል በወረታ ፣ አዘዞ፣ ዳባትና እብናት የአጋዚ ጦር መስፈሩ ተነገረ ። በጎንደር የአገዛዙን ግፍና በደል በመቃወም ህብረተሰቡ ከፍተኛ አመጽና የትጥቅ ትግል እያካሄደ መሆኑ ስርአቱን በእጅጉ አሳስቦታል ።

በተለይም በሰሜን ጎንደር የሚገኙ የነጻነት ሃይሎች በስርአቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው በአካባቢው ከፍተኛ የአጋዚ ጦር እየተሰማራ መሆኑ ተነግሯል ። በዚሁም ምክንያት በሰሜን ጎንደር ህዝቡን የጦር መሳሪያ ለማስፈታት ከፍተኛ የአጋዚ ወታደሮች በአዘዞ ደባት ወረታ እና እብናት እየሰፈሩ መሆናቸው ታውቋል ።

የአጋዚ ወታደሮቹ በሰሜን ጎንደር ያለውን የህዝብ ጦር መሳሪያ ለመግፈፍና ትጥቅ ለማስፈታት ዝግጅት እያደረጉ በመሆናቸው የአካባቢው ህብረተሰብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለኢሳት መረጃውን ያደረሱት የነጻነት ሃይሎች ጥሪ አቅርበዋል ። ህዝቡም ለነጻነት ሃይሎች ድጋፍ በማድረግ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከማድረስ ጀምሮ በመረጃም እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል ።

ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተነሳውን የህዝብ ትግል መቋቋም ያቃተው በህውሃት/ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የአካባቢውን ሰዎች በመግደልና እንዲሰደዱ በማድረግ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም መቆየቱ ይታወሳል ። ትግሉ ግን ከመድከም ይልቅ እየጠነከረ በመምጣቱ የተበሳጨው የህውሃት አገዛዝ የወታደር ክምችቱን ቢያጠናክርም በመጨረሻ አሸናፊ ህዝብ መሆኑን ያመኑት የነጻነት ታጋዮች ስርአቱን እየተፋለሙ ይገኛሉ ።