ባለቤትነቱ የሸህ መሀመድ አል አሙዲ የሆነው የሀዋሳው ሚሊኒየም ፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ ከተዘጋ ሳምንት አለፈው።

ታኅሣሥ  ፭ (አምስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የፋብሪካው ሰራተኞች እንደተናገሩት መንግስት ፋብሪካውን በመዝጋቱ ሳቢያ ከ450 በላይ የሆኑ ስራትኞች በስጋት ተውጠው ይገኛሉ። መንግስት የሸህ አልአሙዲ ንብረት የሆነውን ይህን ፋብሪካ የዘጋው የጥራት ደረጃውን አልጠበቀም በሚል ነው። የፋብሪካውን መዘጋት ተከትሎ ፔፕሲ ኢንተርናሽናል ወደ ስፍራው በመምጣት ባደረገው ምርመራ ፋብሪካው ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ ማረጋገጫ ቢሰጥም መንግስት እንዳይከፈት አዟል ተብሎ ከሳምንት በላይ ታሽጎ ይገኛል። ቀደም ሲል ከታክስ ማጭበርበር ጋርወ በተያያዘ በመንግስትና በሚድሮክ ጎልድ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን ሚድሮክ ለተነሳበት ጥያቄ ሃላፊው ዶክተር አረጋ ይርዳው በዋና ኦዲተር አማካይነት መልስ መስጠታቸው ይታወሳል። የሀዋሳው ፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ የተዘጋው በጥራት ጉድለት አይደለም የሚሉት የድርጅቱ ሰራተኞች ፤ ምናልባት ከዚሁ ከታክስ ጋር በተያያዘ በመንግስትና በሰውየው መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ እንዳላችው ተናግረዋል።