ቢቢሲ በኢትዮጵያ በ3 ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 8/2010)የብሪታኒያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ቢቢሲ/የሚዲያ አፈና ባለባቸው ሀገራት በጀመረው የማስፋፊያ ፕሮግራም መሰረት በኢትዮጵያ በ3 ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የኢትዮጵያና የኤርትራ አድማጮችን ኢላማ ያደረገው የቢቢሲ ፕሮግራም አገልግሎት በኢንተርኔትና በፌስቡክ ይፋ ተደርጓል።

በቀጣይም የሬዲዮ ስርጭት እንደሚጀምር ተገልጿል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው እና በተለያዩ የአለም ቋንቋዎች የሚደመጠው ቢቢሲ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ አድማጮች በ3 ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ቢቢሲ አገልግሎቱን ለጊዜው መስጠት የጀመረው በኢንተርኔት መስመርና በፌስቡክ በኩል መሆኑን አስታውቋል።

በቀጣይነት ደግሞ በኢትዮጵያ በ3ቱም ቋንቋዎች በአጭር ሞገድ በዚህ አመት መጨረሻ የሬዲዮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

የሬዲዮ አገልግሎቱ በእያንዳንዱ ቋንቋ ለ15 ደቂቃ የሚሰራጭ ሆኖ ሌላ ተጨማሪ የ5 ደቂቃ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በሬዲዮ እንደሚሰጥም የአፍሪካ ቢቢሲ የአርትኦት ቡድን ሃላፊ ዊል ሮስ ገልጸዋል።

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ፍራንሲስ አንስዋርዝ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ገለልተኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን የፕሬስ ነጻነት በተገደበባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ማሰራጨቱ ደስታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ አድማጮችን አላማ ያደረገው የቢቢሲ ስርጭት በወቅታዊ ጉዳዮችና ዜና ላይ ያተኩራል።

ከዚህ ባሻገርም በተለይ ወጣቶችን ማእከል ያደረጉ የመዝናኛ፣የስራ ፈጠራና እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች እንደሚካተቱበት የቢቢሲ የስራ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጋዜጠኞች ጋር በመተሳሰር ብቁ ባለሙያ ለማፍራትና ነጻና ገለልተኛ የሚዲያ አውታር ሆኖ ለመስራት መታቀዱንም ነው የተናገሩት።

የቢቢሲ ጋዚጠኞች ስራቸውን በኢትዮጵያ ሲያከናውኑ ከአገዛዙ ባለስልጣናት ፈቃድና እውቅና ስለማግኘታቸውና ምናልባትም ዘገባዎቻቸው የህወሃት መንግስትን ባያስደስቱ ሊደርስባቸው ከሚችለው ችግር እንዴት ሊታደጋቸው እንደሚችል የተገለጸ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም በተለይ የምርጫ 97 ውጤት መጭበርበርን ተከትሎ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት 5 ጋዜጠኞች በሕወሐት መራሹ አገዛዝ በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰሳቸው እና በኋላም በአሜሪካ መንግስት ተጽእኖ ክሱ መነሳቱ ይታወሳል።