በ2002 ዓም ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ወደ ውጭ አገር ባንኮች የተላከው ገንዘብ ፣ መንግስት በተመሳሳይ አመት መድቦት ከነበረው ገንዘብ ጋር እኩል መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ

ህዳር 27 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በ2002 ዓም ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ወደ ውጭ አገር ባንኮች የተላከው ገንዘብ ፣ መንግስት በተመሳሳይ አመት መድቦት ከነበረው ገንዘብ ጋር እኩል መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ይፋ ባደረገው ቅድመ ጥናት መሰረት በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2009 ባሉት 7 አመታት ውስጥ፣ ከ187 ቢሊዮን ብር ወይም 11 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ በውጭ አገር ባንኮች ተቀምጧል።

በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2002 ዓም፣ በአንድ አመት ብቻ ከኢትዮጵያ የተዘረፈው ገንዘብ 3 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን ዶላር ወይም 55 ቢሊዮን ብር ነው።

በ2002ዓም ከኢትዮጵያ የተዘረፈው ገንዘብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በ2001 ዓም ለመደበኛ፣ ለካፒታልና ለክልሎች ድጎማ መድቦት ከነበረው የ54 ቢሊዮን ብር በጀት ጋር ሲነጻጻር፣ የአንድ ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቶአል።

በተመሳሳይም አሐዙ መንግስት በ2002 ዓም  ይዞት ከነበረው የ64 ቢሊዮን ብር በጀት ጋር ሲነጻጸር ፣ የ10 ቢሊዮን ብቻ  ልዩነት አለው።

ከ1993 እስከ 2002ዓም ባሉት አስር አመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ የተዘረፈው አጠቃላይ ገንዘብ መንግስት በያዝነው 2004ዓም ከመደበው 117 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር በ60 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቶአል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት በሙስና ወደ ውጭ ባንኮች የፈሰሰውን ገንዘብ ለመቆጣጠር ተችሎ ቢሆን ኖሮ ፣ የኢትዮጵያ የዚህ አመት በጀት 300 ቢሊዮን ብር ይደርስ ነበር።

የተዘረፈው ገንዘብ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ የገነባችውን መንገዶች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ ጤና ኬላዎች ከሶስት እጥፍ በላይ በሆነ መጠን ለመገንባት ያስችላት ነበር።

የመለስ መንግስት ባለፉት 20 አመታት 80 ቢሊዮን ብር በማውጣት 27 ሺ ኪሎሜትር መንገድ መገንባቱን በኩራት የሚገር ሲሆን፣ ይህ የተዘረፈው ገንዘብ ለመንገድ ግንባታ ውሎ ቢሆን ኑሮ ፣ ግንቦታውን በ3 እጥፍ በማሳደግ 71 ሺ ኪሎሜትር መንገዶችን መገንባት ያስችል ነበር።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፣ ከኢትዮጵያ በአለፉት 10 አመታት የተዘረፈው ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ በምግብ ለስራ ፕሮግራም የታቀፉትን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣  ከ4 ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉትን ወገኖች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ወድቀው በቆሻሻ ገንዳዎች ላይ ምግብ እየለቀሙ የሚኖሩትን ዜጎች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ማስቻል ይቻል እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ህብረሰተቡን እያስመረረ ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስ እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሙስና ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተዘፍቀው ገንዘባቸውን በውጭ አገር ባንኮች በማስቀመጥ ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ጥቂት የህወሀት ጄኔራሎችና ባለስልጣናት ናቸው።

በከፍተኛ ደረጃ ዝርፊያ ከሚካሄድባቸውና የኦዲት መስሪያቤቶችን የምርመራ ውጤት ለመቀበል ፈቃደኛ ከማይሆኑት መስሪያ ቤቶች መካከል ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴር አንዱ ነው።

በጄኔራል ሳሞራ የኑስ የሚመራው መከላከያ ሚኒስቴር፣ ለጦር ጀኔራሎችና ለህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት እቃዎችን ያለቀረጥ እንዲያስገቡ በማድረግ፣ ከፍተኛ ዝርፊያ እንደሚያካሂድ ኢሳት በቅርቡ በሰራው የዶኩመንታሪ ፊልም ማጋለጡ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ጉምሩክ፣  ቴሌኮሚኒኬሽን፣ መብራት ሀይል እና ዋና ዋና የገንዘብ ምንጭ የሆኑ ተቋማትን የተቆጣጠሩት፣ የህወሀት ባለስልጣናት፣ ከመስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየዘረፉ ነው።

አብዛኛቹ ባለስልጣናት ገንዘባቸውን በምስራቅ አገሮች ባንኮች በማስቀመጥ ላይ መሆናቸውንም አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አብዛኛው ዘረፋ የተካሄደው ከምርጫ 97 ወዲህ ሲሆን፣  አሁንም ድረስ ተጡዋጡፎ መካሄዱን የፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ዘገባ ያመልክታል።

 

የአለም መንግስታት በአለም እጅግ ደሀ ከሆነችው እና በምጽዋት ከሚያኖሩዋት ኢትዮጵያ፣ ይህን ያክል ገንዘብ መዘረፉን ከሰሙ በሁዋላ የሚያወጡት መግለጫ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

አቶ መለስ ከጥቂት ወራት በፊት ቱርክ ተገኝተው በነበረት ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከአገራቸው 8 ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ተዘርፎ ወደ ውጭ ባንኮች መግባቱን ገልጠውላቸው ነበር።

አቶ መለስ መረጃውን ሰምተው እንዳልሰሙ በመሆን ምንም መልስ ሳይሰጡ የጉባኤ አዳራሹን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።

አዲሱም ሪፖርት በተባባሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የሪፖርቱ አዘጋጆች ” ኢትዮጵያውያን እዬደሙ ነው በማለት” የዝሪፊያውን አስከፊነት በሪፖርታቸው ላይ አስፍረዋል።