በፍኖተ-ሰላምና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ

ኢሳት (ነሃሴ 19 ፥ 2008)

በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው ፍኖተ ሰላም ከተማ ረቡዕ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ሃሙስ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉንና በትንሹ አንድ ሰው መገደሉን የተተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

የከተማዋ ነዋሪ ለሁለተኛ ቀን አደባባይ በመውጣት የገዢው የኢህአዴግ መንግስት የሆነ ፖስተሮችንና የተለያዩ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ጽሁፎችን ለበርካታ ተቋማት ላይ ሲያወርዱ መዋላቸውን እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመበተን በወሰዱት የተኩስ ዕርምጃ አንድ የኮሌጅ ተማሪ የተገደለ ሲሆን፣ ድርጊቱ በነዋሪው ዘንድ ተጨማሪ ቁጣ መቀስቀሱን ለመረዳት ተችሏል።

የከተማዋ ነዋሪ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመከታተል ለመንግስት መረጃን ሲያቀብል ነበር በተባለ አንድ ታጣቂ የመኖሪያ ቤቱ ቁጣ በተሰማቸው ግለሰቦች እንዲቃጠል መደረጉን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከከተማዋ ወደ ባህር ዳርና ደብረ ማርቆስ የሚወስዱ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ መቋረጡም ታውቋል።

የከተማዋ ነዋሪ በባህር ዳርና እና ጎንደር ከተማ በመካሄድ ላይ ላለው ተቃውሞ አጋርነታቸውን ለማሳየት ሲሉ ረቡዕ ከቤት ያለመውጣትና የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁንና ይኸው አድማ በአደባባይ ተቃውሞ በመታገዝ ላይ ሲሆን፣ የጸጥታ ሃይሎች አድማው እንዲያበቃ የሃይል እርምጃን ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት ሲሳካ አለመቻሉን ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

ሃሙስ በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮች በተካሄደ ተቃውሞ በከተማዋ የመንግስትን ፖለቲካዊ መልዕክትን የሚያስተላልፉ ፖስተሮችና መፈክሮች እንዲወርዱ የተደረገ ሲሆን፣ ባለኮከብ ባንዲራም እየወረደ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ መተካቱን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።

በፍኖተሰላም ከተማ ዙሪያ ባሉ የቡሬና ጅጋ ከተሞች ሃሙስ አዲስ ተቃውሞ መቀስቀሱንና ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር መጋጨታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዶችን በመዝጋት እንዲሁም የተኩስ ዕርምጃን በመውሰድ ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር እየተፋለሙ እንደሆነ ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን ጎንደር ዞን ስር በሚገኙ የደባርቅና ዳባት ከተሞች ነዋሪዎች ሃሙስ ተቃውሞ መጀመራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በከተሞቹ በመካሄድ ላይ ያለውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ ጎንደርና የተለያዩ ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ መቋረጥሉ ታውቋል።

በአማራ ክልል ተጠናክሮ የቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደሩን ደግሞ የክልሉ መንግስት ሃሙስ ይፋ አድሩጓል።

ኣየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መንግስት ሁሉንም ችግሮች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት እንደሚጥር ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።