በፈረንሳይ ቴልኮም ላለፉት ሁለት አመታት ሲተዳደር የነበረው ቴሌ ፣ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ሰራተኞች ተናገሩ

ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የድርጅቱ ሰራተኞች እንደገለጡት 34 የሚሆኑ የፈረንሳይ የቴልኮም ኩባንያ ሰራተኞች የቴሌን ማኔጅመንት ለማሻሻል የ30 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 600 ሚሊዮን ብር በላይ ኮንትራት ቢፋራረሙም በድርጅቱ ላይ ከውድቀት በስተቀር እድገት አልመጣም።

በሁሉም ዘርፎች ያለው አግልግሎት ተዳክሟል የሚሉት ሰራተኞች፣ የቀድሞውን ማኔጅመንት የተካው ከመከላከያ ሚኒስቴር የተውጣጡት የህወሀት የጦር መኮንኖችም ምንም ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም ይላሉ።

በቴሌ ውስጥ ያለው አሰራር ከመበላሸቱ የተነሳ፣ በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ የሚሰጠው አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በባሰ መዳከሙን ሰራተኞች ይናገራሉ።

መንግስት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ከስሮ ምን ለውጥ አመጣ ሲሉ የሚጠይቁት ሰራተኞች፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ስርጭት ባለበት መቆሙን፣ የሞባይል ማስፋፋት ስራም ድሮ ከነበረበት ደረጃ ፈቀቅ አለማለቱን ተናግረዋል።

ቴሌን በህወሀት ወታደራዊ ባለስልጣንት ስር ለማቆየት የተፈለገበት ምክንያት ድሮም ቢሆን ግልጽ ነበር ያሉት ሰራተኞች፣ ምናልባትም በድርጅቱ ውስጥ የተጠናከረ ስራ ተሰርቷል ከተባለ የስልክ መጥለፍ ስራ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቴሌ የተባረሩት ሰራተኞች ወደ ደቡብ ሱዳን እና አረብ አገራት በመሄድ በተሻለ ደሞዝ እየተቀጠሩ መሆኑ ታውቋል።

ብዙዎቹ ሰራተኞች መንግስት በወሰደው ሰራተኛ ቅነሳ ሳይደናገጡ፣ በተሻለ ደሞዝ ክፍያ በአረብ እና በአፍሪካ አገራት ተቀጥረው በመስራት ላይ ናቸው።

አንዳንድ ሰራተኞችም የራሳቸውን ድርጅቶች ከፍተው የተሻለ ስራ እየሰሩ መሆኑን ሰራተኞች ይናገራሉ።