በጋይንት የአርበኛ ግንቦት ሰባት ታጋዮች በብዓዴን ጽ/ቤት ላይ ጥቃት ሰነዘሩ

ኢሳት (መጋቢት 14 ፥ 2009)

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር በጋይንት ከተማ የአርበኛ ግንቦት ሰባት ታጋዮች በብዓዴን ጽ/ቤት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተሰማ።

በከተማዋ የአስተዳደር እና ጸጥታ መረጃ ሃላፊ መኖሪያ ቤት የቦንብ ጥቃት ተፈጽሞበታል። በወገራ ወረዳ እና ሌሎች አካባቢዎች በተሰነዘረው ጥቃት ደግሞ የህወሃት/ኢህአዴግ  ወታደሮች ተገድለዋል። ጥቃቱ የተሰነዘረው በመከላከያና በጸረ-ሽምቅ ሚሊሺያዎችና መደበኛ የፖሊስ አባላት ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ እና ሌሎች አካባቢዎች ባካሄደው ጥቃት የህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች ተገድለዋል።

ጥቃቱ የተሰነዘረው በመከላከያ፣ በጸረ-ሽምቅ ሚሊሺያዎችና መደበኛ የፖሊስ አባላት ላይ መሆኑን ምንጮችን ገልጸዋል። በዚሁ ተከታታይ ጥቃትም አካባቢውን ጥለው የሸሹ የስርዓቱ ታጣቂዎች በርካታ ናቸው ተብሏል።

ንቅናቄው በሰሜን ጎንደር በጀመረው በዚሁ ጥቃት 3 ወታደሮች ወዲያውኑ ሲገደሉ፣ ሌሎች ሃኪም ቤት ከገቡ በኋላ የሞቱም እንዳሉ ምንጮች ይጠቅሳሉ። በተለይ በሰሜን ጎንደር በወገራ ወረዳ ገደብዬ በተባለች ከተማ በተወሰደው የሽምቅ ጥቃት የአካባቢው ፖሊስ ጽ/ቤት ላይ ጉዳት ደርሷል። በከተማዋ የነበሩት የመከላከያ፣ የጸረ-ሽምቅ እና የፖሊስ ሰራዊት አባላት ለጥቃቱ የተኩስ ምላሽ በመስጠታቸው ውጊያው ተጧጡፎ እንደነበር ተገልጿል።

ተኩሱም ለ45 ደቂቃዎች ቆይቷል ተብሏል። በዚሁ 3 የአገዛዙ ታጣቂዎች ሲገደሉ ሌሎች አካባቢውን ትተው በመሸሻቸው የዞኑ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ (ኮማንድ ፖስት) ሃላፊ እጅግ ተበሳጭተው እንደነበር ተነግሯል።

የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊ ከውጊያው በኋላ ስብሰባ ጠርተው የከተማዋን ፖሊስ አዛዥ የጸረ-ሽምቅ ጋንታ መሪና የመከላከያ ቡድኑ አመራሮችን ከስራ ማገዳቸው ተገልጿል። ጥቃቱን ያበሰሩት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋዮችም ወደ መጡበት መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከአርበኞቹ በኩል ስለደረሰው ጉዳት ይተገለጸ ነገር የለም።

በሌላ በኩል በጎንደር ዙሪያ ማክሰኝት ከተማ አካባቢ ዳንጉላ ጭንጫዬ በተባለ ቦታ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሸማቂዎችን ለማጥቃት በተደረገ ጥቃት የአገዛዙ ታጣቂዎች ቆስለው የአካባቢው አመራር የነበረው አበበ ታከለ መገደሉ ተነግሯል።

በጎንደር ሊቦ ከመከም ወረዳ በፈንዲቃ ቀበሌ ደግሞ በጤና ጣቢያውና በት/ቤት ውስጥ ሰፍረው የነበሩ የህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች በአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋዮች ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተቋማቱ ላይም ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። የህወሃት/ኢህአዴግ ታጣቂዎች እርሳቸውን ለማዳን ሲሉ የህዝብ ተቋማት መጠለያ እንደሚያደርጉ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ የመለክታል።