በጎንደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን “እናንሳው አናንሳው” በሚል የህዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ ሙከራ ቢደርገም የህዝቡ መልስ ባለስልጣኖችን አስደንግጧል

የካቲት ፲፬ ( አሥራ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ የጎንደር ቀበሌዎች በተካሄዱ የህዝብ ስብሰባዎች፣ የአገዛዙ ካድሬዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት በኩል የህዝቡ አስተያየት ምንድነው በሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ህዝቡ ግን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ በጽሁፍ ፣ “ እናንትን አንቀበላችሁም፣ አናውቃችሁም፣ ከህዝብ ውጭ ሆናችሁዋል” የሚል መልስ በብዛት መስጠቱ ካድሬዎችን አስደንግጧል።

አንዳንድ ሰዎች “ አዋጁን ስታውጁ እኛን አላማከራችሁንም፣ ሁሌም በራሳችሁ ከላይ ወስናችሁ ከጨረሳችሁ በሁዋላ ነው እኛን የምትጠይቁን፣ እኛ ደግሞ ኮማንድ ፖስት ተነሳ አልተነሳ ከግድያና አፈና አትታቀቡም፣ ብትፈልጉ አንሱት ባትፈልጉ ተውት፣ ጥቅሙን መጨረሻ ላይ ታገኛላችሁ” የሚሉ አስተያየቶችም በብዛት ተሰጥተዋል።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ “ መምራት ተስኖአችሁዋል፣ ብቃት የላችሁም፣ እናንተ በአንድ ክልል ሰዎች ነው የምትመሩት” የሚሉ መልሶችም የተሰጡ ሲሆን፣ በተለይ “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ በሁሉም አካባቢዎች የተሰጠው መልስ አንድ አይነት መሆኑ ካድሬዎችን አስገርሟል።
አብዛኞቹ ተስብሳቢዎች ከንግግር በሁዋላ የሚመጣባቸውን በመፍራት ለመናገር ፈቃደኞች ያልሆኑ ሲሆን፣ መልሶቻቸውን በጽሁፍ በመስጠት ስሜታቸውን ገልጸዋል። በቅርቡ የፌደራል የኮማንድ ፖስት አመራሮች በአማራ ክልል ያለውን የህዝብ ስሜት ካጠኑ በሁዋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ለሌላ ዙር ተቃውሞ የሚጋብዝ በመሆኑ ፣ አዋጁ እንዳይነሳ እንመክራለን ማለታቸውን ኢሳት ዘግቦ ነበር። ይህን ጥናት በመያዝ በቀጥታ ህዝቡን ለማናገር የተደረገው ሙከራም፣ ህዝቡ ከአገዛዙ ጋር መለያየቱን የሚያሳይ ሆኗል።
አብዛኛው የጎንደር ባለሃብቶች ግብር ባለመክፈል እና አስተዳዳራዊ በሆኑ ጉዳዮች ባለመሳተፍ ተቃውሞአቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።