በጎንደር የቦንብ ፍንዳታ ተከሰተ

ሚያዝያ ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ የቦንብ ፍንዳታን ባስተናገደችው ጎንደር፣ ማክሰኞ ምሽት 2 ሰአት አካባቢ ታክሲ ማዞሪያ በጌምድር ሆቴል አካባቢ ቦንብ መፈንዳቱን የአይን እማኞች ተናግረዋል። በፍንዳታው በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱን የሚገለጹት እማኞች፣ በፍንዳታው ወቅት ከፍተኛ ድምጽ ከመሰማቱ ጋር ተያይዞ በአካባቢ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር ብለዋል።
የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከ15 ደቂቃ በሁዋላ ወደ አካባቢው በመምጣት መንገዶችን በመዝጋት መንገድ ላይ ያገኙዋቸውን ሰዎች ይዘው አስረዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
በሌላ በኩል አርበኞች ግንቦት 7 ሚያዚያ 8 ቀን 2009 ዓም በትክል ድንጋይ እና በወገራ መሃል ልዩ ስሙ ጭጋሳ ቀበሌ ላይ ሳጅን ያለውቀን አበበ እና ኮንስታብል ሙሉጌታ የተባሉትን የፖሊስ አባላትን አፍኖ መውሰዱን ለኢሳት በላከው መረጃ አስታውቋል።
ስለታፈኑት ፖሊሶች የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማናገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል የጸጥታ ስራ ለመስራት ለክልሉ ፖሊሶችና ለክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ተሰጥቶ የነበረው ስልጣን በኮማንድ ፖስቱ እንዲወሰድ ከተደረገ በሁዋላ፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት አመኔታ አጥተው ከጥቅም ውጭ መደረጋቸውንና ማንኛውም ውሳኔ በህወሃት በሚመራው ኮማንድ ፖስት እንደሚሰጥ የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል።
ፖሊሶች “ለኮማንድ ፖስቱ ታማኝ የሆኑና ያልሆኑ” በሚል መከፈላቸው እርስ በርስ እንዳይተማመኑ አድርጓቸዋል። የፖሊስ ሙያ ገለልተኛ ነው ፣ በወታደራዊ እዝ ሊመራ አይችልም የሚሉ አስተያየቶችን ያቀረቡ ፖሊሶች የተለያዩ ሰበቦች እየተፈጠሩላቸው ከስራ እንዲሰናበቱ ወይም በፈጠራ ወንጀል እንዲታሰሩ እየተደረገ ሲሆን፣ የኮማንድ ፖስቱን ተእዛዝ አሜን ብለው የሚቀበሉ ደግሞ የደረጃ እድገት እየተሰጣቸው ነው።
እንደ ምንጮች መረጃ ኮማንድ ፖስቱ፣ “የክልሉ አመራር በክልሉ ውስጥ የሚታየውን የጸጥታ መደፍረስ እንዲቆጣጠር ስልጣኑን ከመመለሳችን በፊት ፣ የለውጥ ሃይሎችን የሚደግፉት አብዛኞቹ ፖሊሶች ግምገማ ተካሂዶ እንዲባረሩ ይጠይቃል። አሁን ያሉት ፖሊሶች በሚያሳዩት አቋም ፣ የክልሉን ጸጥታ የማስከበር ስራ እንዲሰሩ መፍቀድ ማለት ከወራት በፊት የታየውን ህዝባዊ አመጽ እንዲደገም ማድረግ ነው በሚል፣ ቁጥጥሩን ለክልሉ ባለስልጣናት ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆኑን ግልጽ አድርጓል።
በዚህም የተነሳ የአማራ ክልል ባለስልጣናት በክልላቸው ውስጥ ስለሚደረገው ነገር ምንም መረጃ እንደሌላቸውና ተንሳፈው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።