በጎንደር ከተማ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ አንደኛ አመት በከተማዋ እየታሰበ ነው

ሐምሌ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- “የወልቃይት የአማራ ማንነት ይከበር” በሚል መነሻ የተጀመረው ህዝባዊ እንቅስቀሴ ወደ አጠቃላይ የመብት እና የእኩልነት ጥያቄዎች ተሸጋግሮ፣ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዊ ዞን ከፍተኛ ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አመጹ የተጀመረበትን ቀን ለመዘከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው። ይህ ህዝባዊ አመጽ የስርዓቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉን ተከትሎ፣ አገዛዙ አመቱን በሙሉ አገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በወታደራዊ አገዛዝ ለመግዛት ተገዷል።
የጎንደር ከተማ ህዝብ ቀኑን በቤተክርስቲያን በመገኘት የሻማ ስነስርዓት በማድረክ ዘክሯል። ወታደሮች፣ የብአዴን እና የህወሃት የደህንነት አባላትም ሲቪል በመልበስ ሲንቀሳቀሱ ውለዋል። በአቦ ቤተክርስቲያን አርማ የሌለው የኢትዮጵያ ባንዲራ እንደተሰቀለ ወታደሮች ሲያስወርዱ ህዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል።
ቀኑ በማህበራዊ ሚዲያዎችም እየታሰበ ነው።
የወልቃይት ማንነት አስከባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ለመያዝ ከትግራይ ክልል የመጡ ታጣቂዎች ከደህንነት አባላት እና የአጋዚ ወታደሮች ጋር በመሆን ኮሎኔሉን አፍነው ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ በህዝቡ ተሳትፎ መክሸፉ ይታወሳል።
በኦሮምያና በአማራ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ለመቆጣጠር አገዛዙ ከፍተኛ የሆነ ሃይል በመጠቀሙ ከ1 ሺ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል።