በጎንደር አምባ ጊዮርጊስ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጊዜ የታሰሩ 14 ሰዎችን አስለቀቁ

ኢሳት (ነሃሴ 12 ፥ 2008)

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር አምባ ጊዮርጊስ ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሃሙስ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በቅርቡ ለእስር የተዳረጉ 14 ነዋሪዎችን በከተማዋ ከሚገኝ እስር ቤት በሃይል ማስለቀቃቸውን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

የከተማዋ ነዋሪዎች ሰኞ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኘተው ያላቸው ጥያቄ እንዲሰሙ ያቀረቡትን ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ሃሙስ ተቃውሞን ሲገልጹ መዋሉን ለመረዳት ተችሏል።

ነዋሪዎቹ ሰኞ ለከተማው አስተዳደር ባቀረቡት ጥያቄ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ሃሙስ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ማንም የመንግስት አካል ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት በርካታ የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎችን በዕለቱ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሄዱ ማርፈዳቸውን እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።

በዕለቱም በቅርቡ ከተካሄደ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር ከተዳረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል 14 ሰዎች ከአንድ ፖሊስ ጣቢያ በነዋሪው በሃይል እንዲለቀቁ መደረጉን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ የወሰዱትን ድርጊት ተከትሎ በከተማዋ ዙሪያ የነበሩ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ወደ ፖሊስ ጣቢያው ቢመጡም ምንም እርምጃ ሳይወስዱ መመለሳቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እስረኞቹን ከማስለቀቅ በተጨማሪ ባለ ኮከብ ባንዲራ ከአንድ የከተማ አስተዳደር ቅጥር ግቢ በማወረድ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ መተካታቸውን እማኞች አክለው አስረድተዋል።

ሃሙስ ሲካሄድ በቆየው በዚሁ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ነዋሪዎች አራት የወረዳ አስተዳዳሪዎችን በማገት አቋማቸውን ለህዝብ እንዲያሳውቁ በማሳሰብ ቀነገደብ ሰጥተዋቸው እንደለቀቋቸው ታውቋል።

ለሁለተኛ ጊዜ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት የአመባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች መንግስት ለወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ እልባትን የማይሰጥ ከሆነ፣ “ራሳቸውን በማደራጀት” የጀመሩትን ትግል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ስገልጹ ማርፈዳቸውን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አክለው ገልጸዋል።