በጎንደርና በባህርዳር ከተሞች የደረሱት የቦምብ ፍንዳታዎች በቱሪዝም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላል ተባለ

ኢሳት (ጥር 5 ፥ 2009)

በአማራ ክልል በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች ሰሞኑን የደረሰው የቦምብ አደጋ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል አንድ አለም አቀፍ የደህንነት ተቋም አርብ ገለጸ።

በመከላከያና የደህንነት ዙሪያዎች የሚሰራውና አይ ኤች ኤስ (IHS)  ጄንስ 360 የሚል መጠሪያ ያለው ይኸው ተቋም ሁለቱ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ አለም አቀፍና የሃገር ውስጥ ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱ በመሆኑ አደጋው ለቱሪስቶቹ የደህንነት ስጋት ሊያሳድር እንደሚችል አስታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱን ያወሳው የደህንነት ድርጅቱ አለመረጋጋቱ ዕልባት ሳያገኝ ከቀናት በፊት በሁለት ሆቴሎች ላይ የደረሰው የቦምብ አደጋ በቱሪስቶች እንዲሁም ወደ አካባቢው ለተለያዩ ጉዳዮች በሚጓዙ አካላት ዘንድ ተደራራቢ ስጋት ማሳደሩን ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

የአሜሪካና የብሪታኒያ መንግስታት በሁለቱ ከተሞች የደረሰውን የቦምብ አደጋ ተከትሎ ለዜጎቻቸው የጉዞ ማሳሰቢያን ማሰራጨታቸው ይታወሳል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማንኛውም የኤምባሲው ሰራተኛ ወደ ጎንደር ከተማ እንዳይጓዝ እገዳን ተግባራዊ ማደረጉ የሚታወቅ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የሃገሪቱ ዜጎች በአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ቢጓዙ የደህንነት አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል በማሳሰብ በጉዞአቸው ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ሃገሪቱን ለመጎብኘች አቅደው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፓ ቱሪስቶች ጉዟቸውን መሰረዛቸው የሚታወስ ነው።

በአዋጁ ምክንያት በተያዘው አመት ሃገሪቱን የሚጎበኙ አለም አቀፍ ቱሪስቶች በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች የደረሰ የቦምብ አደጋም ይህንኑ ችግር ያጠናክረዋል ሲል የደህንነት ተቋሙ አክሎ ገልጿል።

ማክሰኞ ምሽት ጎንደር ከተማ በሚገኘው ኢንታሶል ሆቴል ላይ በደረሰው የቦምብ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና 18 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና የተለያዩ መገኛኛ ብዙሃን እንዲሁም የአሜሪካና የብሪታኒያ መንግስታት በአደጋው ስድስት ሰዎች ላይ ብቻ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል። ፖሊስ አደጋውን ፈጽመዋል ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።