በግብር ጭማሪ የተነሳውን ተቃውሞና አድማ እንደቀጠለ ነው

በግብር ጭማሪ የተነሳውን ተቃውሞና አድማ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 20/2009)በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት በመላ ሀገሪቱ የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የሃይል ርምጃን ብቸኛ አማራጭ ማድረጉ ይነገራል።

በአዲስ አበባ በመርካቶ ባለፈው ሰኞ የተዘጉትን ሱቅና መደብሮች ለማስከፈት ከፖሊሶች በተጨማሪ የደህንነት ሃይሎች በየሱቆቹና መደብሮቹ በመዘዋወር ነጋዴውን ሲያስፈራሩ እንደነበር የኢሳት ዘጋቢ ከስፍራው ገልጿል።

የነጋዴው ቅሬታ ሳይሰማ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ በሃይል በማስፈራራት የተዘጉት ሱቆችና መደብሮች መከፈታቸውን ዘጋቢያችን ጨምሮ ጠቅሷል።በአዲስ አበባ ወረዳ 9 ቀጠና 2 የተጠራውና ነጋዴውን ለማነጋገር የታቀደው ስብሰባ የፖለቲካ አባላት የሆኑትን በማስቀረት ሌሎች አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ ተደርጎ መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል።

ስብሰባው በግብር ጉዳይ ላይ ቢሆንም አዳራሹ ውስጥ የነበሩ የመንግስት ሃላፊዎች የፖለቲካ አባል ያልሆኑትን እየለዩ ማስወጣታቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በግብር ላይ የተነሳው ተቃውሞ ጠንከር ብሎ እየተካሄደባቸው ካሉ አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ጎጃም ነው።በሸበል በረንታ የተጀመረው አድማ ከደብረማርቆስ በቀር አብዛኛውን አካባቢ እንደነካካው ከሚደርሱን መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።

በሞጣ የነጋዴው አድማ በአራተኛ ቀን ውሎው ቀጥሏል።በአድማው ያልተሳተፉትን በመጨመር በከተማዋ ከእንቅስቃሴ ውጪ የሆነ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

ዛሬ በደረሰን መረጃ በሞጣ ሙሉ በሙሉ የስራ ማቆም አድማው ተምቷል።የተከፈተም የንግድ ቦታም የለም።

የወረዳው የሚሊሻ ዘርፍ ሃላፊ ሽጉጥ ይዘው በየመደብሩ በመሄድ አስፈራርተው ለማስከፈት ያደረጉት ወከባ በህብረተሰቡ ቁጣ ሊሳካ እንዳልቻለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።የሞጣ ህብረተሰብም አቋም ወስዷል በአድማው ለመቀጠል ተስማምቷል።

በምስራቅ ጎጃም ከሞጣ በተጨማሪ ብቸና ፣መርጦ ለማርያምና ሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ የአድማ ርምጃ መወስዳቸው ታውቋል።

በኦሮሚያ ጅማና ሻምቡ አድማውን ከቀጠሉት አካባቢዎች ይጠቀሳሉ።በጅማ ከተጀመረው አድማ ጋር ስለ መያያዙ ባይገለጽም ትላንት ምሽት የቦምብ ጥቃት በከተማዋ ከንቲባ መኖሪያ ቤት መፈጸሙ ታውቋል።

ነጋዴው ለቀናት በአድማ መቆየቱ ስጋት የገባቸው የስርአቱ ደህንነቶች ሆን ብለው የፈጸሙት ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።

የቦምብ ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት የታወቀ ነገር የለም።የአድማውን እንቅስቃሴ ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር በማያያዝ ነጋዴዎችን ለማሰር ተፈልጎ ሳይሆን እንደማይቀር ታዛቢዎች ይናገራሉ።