በጋሞ ጎፋ ዞን ባለው ድርቅ ሰዎችና እንስሳት ህይወታቸው እያለፈ ነው

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች፣ አርሶአደሮች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንስሳት ያለቁ ሲሆን፣ ሰዎችም መሞት ጀምረዋል። ድንችና የመሳሰሉት ሰብሎች በዝናብ እጥረት መጥፋታቸውን የሚገለጹት ነዋሪዎች፣ በሴፍትኔት እንዲታቀፉ ለተደረጉ ካድሬዎች እህል ቢከፋፈልም አብዛኛው ህዝብ እርዳታ ባለማግኘቱ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል።
በድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቁት መካከል ኮንሶ፣ ደራሸ፣ ጨንጫ፣ ጊታ፣ ካምባ፣ ደረማሎና ቁጫ የሚገኙበት ሲሆን፣ በአመቱ ውስጥ ዝናብ ለሁለት ቀናት ብቻ መዝነቡን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ከሁለት ሳምንት በፊት ለ 2 ቀናት የዘነበው ከባድ ዝናብም ጭንጫ ላይ ብቻ ከአንድ ቤተሰብ 3 ህጻናትን ከመግደሉም በላይ ከፍተኛ የሆነ ንብረትም አውድሟል።
የአካባቢው ህዝብ ለአባይ ግድብ በሚል የቦንድ ግዢ እንዲፈጽም፣ የአባይ ዋንጫ ምርቃት በሚል ገንዘብ እንዲያዋጣ እየተገደደ ሲሆን፣ ከአመታዊ ግብር ክፍያው ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ስቃይ ተደርጓል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት ድርቁን ተከትሎም ታዋቂው የአርባምንጭ ደን እየተጨፈጨፈ ለመጥፋት ተቃርቧል። ከ500 በላይ የሚሆኑ አርሶአደሮች ደኑን እየቆረጡ ለከተማው ህዝብ የማገዶ ፍጆታ በመሸጥ ላይ ናቸው።
እጅግ አሳዛኙ ነገር የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በእየለቱ ለምግብ ዝግጅት የሚጠቀምበትን ከፍተኛ ማገዶ ከደኑ እያስቆረጠ መጠቀሙ ለደኑ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ለከተማው ምንጮች መድረቅም መንስኤ እየሆነ መምጣቱ ነው።
የኑሮ ውድነቱም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ቀድሞ በኪሎ ሁለት እና ሶስት ብር ይሸጥ የነበረ በቆሎ 10 ብር እየተሸጠ ይገኛል፣ ከ 500 እስከ 600 ብር ይሸጥ የነበረው ጤፍም 2500 ብር ደርሷል ይላሉ ነዋሪዎቹ። “በጡረታ የሚተዳደሩ፣ ቋሚ ገቢ የሌላቸው ሰዎች ሁሉ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኖአቸው ሞት አፋፍ ላይ ይገኛሉ” የሚሉት ነዋሪዎች፣ በአካባቢያቸው እንዲህ አይነት አስከፊ ጊዜ አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።