በጋምቤላ 20 የኦሮሞ ተወላጆች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ታሰሩ

ነሃሴ  ፲ ( አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ በመካሄድ ላይ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ 20 የኦሮሞ ተወላጅ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች አምልኮ ከሚያደርጉት ቤተክርስቲያን ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። በእጃቸው ላይ ከመጽሃፍ ቅዱስ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ያልያዙት አማኞች፣ ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ መታሰራቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቤተክርስቲያን ምንጮች ገልጸዋል። ሰዎቹ ለአንድ ሳምንት ያክል በጋምቤላ እስር ቤት ሲቆዩ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አልተደረገም። የአያያዛቸው ሁኔታ መጥፎ መሆኑን የሚናገሩት እነዚህ ምንጮች፣ በአጠቃላይ በጋምቤላ መንግስት አለ ብሎ መናገር አይቻልም ይላሉ።

በመላ አገሪቱ እየታዬ ያለው ውጥረት በጋምቤላም በተመሳሳይ ሁኔታ እየታየ መሆኑንና ሁኔታው እየከፋ መምጣቱ ይገልጻሉ።  ተቃውሞውን ተከትለ የታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆች በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።