በጋምቤላ ክልል በአውቶቡስ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 5 ሰዎች ተገደሉ

ኢሳት (ታህሳስ 20 ፥ 2009)

ከጋምቤላ ከተማ ወደ መታር ከተማ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞበት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ  አስታወቀ።

በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ረቡዕ ጠዋት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ከጋምቤላ ክልል 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መሆኑ ታውቋል።

አውቶቡሱ ከ40 በላይ መንገደኞች አሳፍሮ ነበር ።

ማንነታቸው አልታወቀም የተባሉት ታጣቂዎች የተሽከርካሪውን የነዳጅ መያዣ በጥይት በመቱት ጊዜ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተነስቶ የአምስቱ መንገደኞች ህይወት ወዲያውኑ ሊያልፍ መቻሉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ዘጠኝ መንገደኞች ላይ ቀላልና ከባድ የመቁሰል ጉዳት መድረሱንም ፖሊስ አስታውቋል። ይሁንና ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉት ታጣቂዎች ከስፍራው  አምልጠዋል።

ታጣቂዎቹ በዳረሱት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው መንገደኞች በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የተጠቁ አካላት በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወሳል።

ባለፈው አመት ከደቡብ ሱዳን ሰርገው ገብተዋል የተባሉት ታጣቂዎች ከ100 በላይ ነዋሪዎች ገድለው ከ140 የሚበልጡ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸው መዘገቡ ይታወሳል። ከተወሰዱት ከፊሎቹ ቢለቀቁም፣ የቀሩት አሁንም ዱካቸው አልተገኘም።

ረቡዕ በጋምቤላ ክልል በአንድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ስለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም።