በጋምቤላ ክልል መሬት ተነጥቀው የነበሩ 186 ባለሃብቶች በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ትእዛዝ ተመለሰላቸው

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 11/2009) በጋምቤላ ክልል መሬት ተነጥቀው የነበሩ 186 ባለሃብቶች በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ትእዛዝ ተመለሰላቸው።

በክልሉ ከነበሩ 6መቶ ያህል ኢንቬስተሮች የያዙትን መሬት በአግባቡ አላለሙም በሚል 296 ያህሉ ይዞታቸውን በጋምቤላ መስተዳድር ተነጥቀው ነበር።
ባለሃብቶቹ ይህንኑ በመቃወም ቅሬታ በማቅረባቸው በአቶ አርከበ እቁባይ የተመራው አጣሪ ኮሚቴ በተለይ የትግራይ ባለሃብቶች ናቸው ለተባሉት 186 ባለሃብቶች መሬታቸው እንዲመለስ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ባለው ህግ መሰረት የመሬት ሊዝ ኮንትራትን ማስተዳደር የሚችሉት ክልሎች ናቸው።

በጋምቤላ ክልል መሬትን ለኢንቨስትመንት ወስደው አላለሙም የተባሉትን 296 ባለሃብቶች ይዞታቸውን የነጠቀውና እንደገና እንዲመለስ ያደረገው ግን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሆኑ ታውቋል።–የክልሉን ስልጣን በመንጠቅ።
በጋምቤላ ካሉ 6መቶ የእርሻ ባለሃብቶች 296 የሚሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተቋቋመውና በአቶ አለማየሁ ተገኑ ይመራ በነበረው አጥኚ ኮሚቴ መሬታቸው መነጠቁ ይታወሳል።

ባለሃብቶቹ መሬታቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተፈቀደላቸው ብድርም ተሰርዞባቸው ነበር።
አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የሆኑት እነዚሁ የጋምቤላ ባለሃብቶች ከፍተኛ ቅሬታ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአጥኚው ኮሚቴ ላይ በማቅረባቸው ሌላ አጥኚ ኮሚቴ በአቶ አርከበ እቁባይ እንዲመራ ተደርጎ ጉዳያቸው እንደገና እንዲታይ መደረጉ ታውቋል።

በዚሁም መሰረት ቅሬታቸውን እንደገና ያቀረቡት ከ296ቱ መካከል 190ዎቹ ብቻ ነበሩ።
የነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ከ4ቱ በስተቀር የ186ቱ ባለሃብቶች መሬት እንዲመለስ ተድርጓል።

ይህም የተደረገው መሬቱን የተነጠቁት ያለአግባብ ነው በሚል እንደሆነ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
በዘገባው እንደተመለከተውም ባለሃብቶቹ መሬቱን በአግባቡ ያላለሙት በመሬት መደራረብ፣በፍርድ ቤት እገዳና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ነው።

ይህም ሆኖ ግን በአቶ አለማየሁ ተገኑ የተመራው የጥናት ኮሚቴ ባለሃብቶቹ የተበደሩትን ገንዘብ በመቀሌና በአዲስ አበባ ህንጻ ሰርተውበታል ከታለመለት አላማ ውጭም አውለውታል ማለቱ ይታወሳል።

ይህ ተዘንግቶ በአቶ አርከበ እቁባይ የተመራውና 13 አባላት ያሉት ኮሚቴ ባለሃብቶቹ ተበድረዋል በሚል መሬቱን የጋምቤላ ክልል ለባለሃብቶቹ እንዲመልስ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል ትእዛዝ እንዲሰጥ አድርጓል።
እስካሁንም የ27ቱ ባለሃብቶች መሬት ሲመለስ የቀሪዎቹም ይቀጥላል ተብሏል።

በልማት ባንክ በኩል የታገደባቸው ብድር እንደገና እንዲለቀቅላቸውም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።