በጋምቤላ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ውይይት ላይ ናቸው

መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ ዜናዊ የጸጥታና የደህንነት አማካሪ የሆኑት አለቃ ጸጋየ በርሄ፣ የልዩ ሀይል ዋና አዛዥ እና የጽረ ሽብር ግብረሀይል ከክልሉ ፕሬዚዳንት ከአቶ ኦሞድ ኦቦንግ ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።

የመለስ መንግስት ባለስልጣኖች ወደ አካባቢው የተጓዙት በጋምቤላ የታየውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ ነው። በክልሉ ሰሞኑን 19 ሰዎች ከተገደሉና 8 ሰዎች ከቆሰሉ በሁዋላ ከፍተኛ የሆነ የፍርሀት ድባብ ነግሷል። በክልሉ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች በመከላከያ ሰራዊት ከሚጠበቁት ከሼክ ሙሀመድ አላሙዲና ከሳውዲ ስታር ኩባንያ ሰራተኞች በስተቀር እንቅስቃሴ አቁመዋል።

በትናንትናው እለት የክልሉ ባለስልጣናት የጋምቤላ ኮሌጅ ተማሪዎችን ሰብስበው ኮሌጁን ትተው ወደ አካባቢያቸው የተጓዙ ተማሪዎች ተመልሰው የሚመጡበት ሁኔታን ለመፍጠር ምክክር አድረገዋል። በጋምቤላ ኮሌጅ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ኮሌጁን ጥለው የወጡት አሁን ባለው የጸጥታ መደፍረስ ትምህርታችንን ለመከታተል አንችልም በማለት ነው። የጋምቤላ የጸጥታ  መደፍረስ  በአለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሆኖ እያለ ተማሪዎች ትምህርት አንማርም ብለው መሄዳቸው ፖለቲካዊ ተጽኖ የሚኖረው በመሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ የማግባባት ስራ እንዲሰሩ ባለስልጣናቱ ጠይቀዋል።

አለመረጋጋቱና ፍርሀቱ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ በመጣባት ጋምቤላ፣ ሰዎች ከስራ ወጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በታክሲ ለመጓዝ ሲጋፉ ይታያሉ። በከተማዋ ማንም ሰው ጸሀይ ዘቅዘቅ ማለት ስትጀምር መንገድ ላይ እንደማይታይ ዘጋቢያችን ገልጧል።

በጋምቤላ የተፈጠረው ችግር መንስኤ የመለስ መንግስት ህዝቡን በጉልበት እያፈናቀለ በሰፈራ ጣቢያዎች በማሰባሰብ መሬቱን ለባለሀብቶች ነጻ በሚባል ዋጋ በመሸጡ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢታንግ ወረዳ መምህራን ደሞዝ እስከዛሬ ያልተከፈላቸው በመሆኑ ትምህርት ቤቶችን መዝጋታቸው ታውቋል።

ኢሳት በጋምቤላ የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስ በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide