በጋምቤላ አሁንም ትምህርት አልተጀመረም

መጋቢት ፳፪ (ሃይ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ የተጀመረው የመምህራን የስራ ማቆም አድማ በመቀጠሉ እስከ ትናንት ድረስ ትምህርት አልተጀመረም። ኢሳት የክልሉ መምህራን ላለፉት ሁለት ወራት ባጀት የለም በሚል ምክንያት ደሞዝ ሊከፈላቸው ባለመቻሉ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን መዘገቡ ይታወሳል። የጋምቤላ ወኪላችን እንዳለው እስከ ትናንት ድረስ በወረዳው የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርት ቤቶች ስራ ያልጀመሩ ሲሆን በቶሎ ስራ ይጀምራሉ ተብሎም አይታሰብም።

የጋምቤላ ኮሌጅ ከሶስትን ሳምንት በፊት ትምህርት መጀመር የነበረበት ቢሆንም 19 የሚሆኑ ተማሪዎች በታጣቂዎች ከተገደሉ በሁዋላ ተማሪዎች ትምህርት ለመጀመር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አሁንም እንደተዘጋ ነው። ከአጎራባች ከተሞች የሚመጡ ተማሪዎች የጸጥታው ጉዳይ አስተማማኝ ባለመሆኑ ትምህርት ለመጀመር ፈቃደኞች አንሆንም በማለታቸው የአቶ መለስ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አለቃ ጸጋየ ሳይቀሩ ተማሪዎችን ለማግባባት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታጣቂዎች ጥቃቱን የሚፈጽሙት ከደቡብ ሱዳን በመነሳት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው መንግስት በጋምቤላ ከተማ ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የሚያደርገውን ስብሰባ ቀጥሎአል። ለዚሁ ስብሰባ ትናንት የአቶ መለስ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አለቃ ጸጋየ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያምና ምክትላቸው እንዲሁም የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋምቤላ ገብተዋል። ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለባለስልጣኖቹ ከፍተኛ የሆነ አቀባባል እንደተደረገላቸው በፎቶ ግራፍ አስደግፎ የላከው ዘገባ ያሳያል። የአሁኑ አቀባበል ከዚህ ቀደም ያልታየ መሆኑን የገለጠው ዘጋቢአችን ምክንያቱም ስልጣኔን አጣለሁ ብሎ የሰጋው ፕሬዚዳንቱ መሪዎቹን ለማባባል ወይም የደቡብ ሱዳን ተዳራሪዎች ድርድሩን የሚካሂዱት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መሆኑን እንዲያውቁት ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ግምቱትን አስፍሯል።

የአካባቢው ህዝብ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ መሆን አለበት የሚባለው የክልሉ ፕሬዚዳንት ኦሞድ ኦቦንግ ከስልጣን እንዲወርድ ሰሞኑን በተካሂዱት ስብሰባዎች ላይ ሲገልጥ ቆይቷል። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ካልወረደ ተደጋጋሚ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በማለት ህዝቡ በስብሰባዎች ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ዛሬ ዝግ ስብሰባ እያካሄዱ በመሆናቸው ስለብሰባ ውጤት ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት አልቻልም። ይሁን እንጅ ጋምቤላ አሁንም በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ስር መሆኑዋ የአካባቢው ችግር በቀላሉ ሊፈታ እንደማይችል የሚያመለክት መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide