በጋምቤላ፣ቤንሻንጉል፣ደቡብ ኦሞና ሌሎች አካባቢዎች በግብርና የተሰማሩ ባለሃብቶች ችግር ገጠመን አሉ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 17/2009)በጋምቤላ፣ቤንሻንጉል፣ደቡብ ኦሞና ሌሎች አካባቢዎች በግብርና የተሰማሩ ባለሃብቶች አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳጋጠማቸው ገለጹ።
ልማት ባንኩን ጸረ ልማት ባንክ በማለት ፈርጀውታል።
የጋምቤላ እርሻ ኢንቨስተሮች ማህበር፣የቤንሻንጉል ጉምዝ እርሻ ኢንቨስተሮች ማህበር፣የደቡብ ኦሞና ጋሞጎፋ ኢንቨስተሮች ማህበር፣የሶማሌ የእርሻ ኢንቨስተሮች ማህበርና ሌሎች በአካባቢው የተሰማሩ ማህበሮች ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት የአቤቱታ ደብዳቤ አጋጠመን ያሉትን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲሁም ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በማለት በደብዳቤያቸው ከዘረዘሩት መካከል በየጊዜው የፖሊሲና መመሪያዎች መለዋወጥ፣የመልካም አስተዳደር መጓደል፣በእርሻ አካባቢያቸው የጸጥታ ችግር መኖር፣በየአካባቢው ለሚያቀርቡት አቤቱታ ምላሽ የሚሰጥ ማጣትና በሶስተኛ ወገኖች የሚፈጸም የመሬት ወረራ የሚሉት ይገኙበታል።
ማህበራቱ ጸረ ልማት አቅጣጫ የሚከተል በማለት ክስ ያቀረቡበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያወጣቸው የብድር ፖሊሲዎች፣መመሪያዎችና የአፈቃቀድ ሒደቶች ስራቸውን ከማደናቀፍ በተጨማሪ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና ለማለፍ ፍላጎት፣ቅንነትና ቁርጠኝነት የተላበሱ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ባንኩ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ርምጃዎች የሚወስደው በኢትዮጵያ ውስጥ በፖሊሲ ባንክ ደረጃ ተወዳዳሪ የግል ባንኮች ባለመኖራቸው እንደሆነ በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።
ልማት ባንክና ንግድ ባንክ በሀገር ደረጃ የብድር ስርአቱን ለመቀየር ወይም የተሰጡ ብድሮች ሳይበላሹ ለማስመለስ ፍላጎት ኖሯቸው አዲስ ፖሊሲ ለማውጣት ተገደው ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያ ስራቸው መሆን የነበረበት ከልማትና ንግድ ባንኮች 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለአምስት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ያበደሩትን ገንዘብ ያስመልሱ ነበር በማለት በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ባንኮቹ ባለባቸው ውስጣዊ የፓርቲ ፖለቲካ ሽኩቻ በታሸ እምቅ ፍላጎት ውስጥ ተጸንሶ የተወለደው አዲሱ ፖሊሲና መመሪያ ዋነኛ ግቡ ልማት ሳይሆን ጭቃ ውስጥ ገብተው ለመውጣት መራጨት ላይ ባሉ አስፈጻሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረት ግብ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእርሻው ዘርፍ ሲሰጥ የነበረው ብድር እንዲቆም መደረጉ ተገቢ አይደለም ያሉት ማህበራቱ ባንኩ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ማበደሩ የሚታወቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ንግድ ባንኩ የሰጠው ብድር ከህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ ጀምሮ የተዘረፈ መሆኑ የአደባባይ ወሬ በሆነበት ሁኔታ ተጠያቂ የሆነ የንግድ ባንክ ሀላፊም ሆነ ባንኩ እንዲያበድር አቅጣጫ ያስቀመጠ የፖለቲካ ሃላፊ የለም በማለት አስታውቀዋል።
ንግድ ባንክ የሰጠውን ብድር መከታተልና ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት እየታወቀ በፖለቲካ ሽፋን ከተጠያቂነት በማምለጥና ጉዳዩን ወደ ልማት ባንክ በድፍኑ ለማስተላለፍ መሞከር የጊዜ ጉዳይ እንጂ በውጭ ባለሃብቶች በተሰጠው ብድር ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ የመሆናቸው ጉዳይ አይቀሬ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
በጋምቤላ በእርሻ መስክ ከተሰማሩ የሐገር ውስጥ ባለሃብቶች 75 በመቶ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን የኦክላንድ ኢኒስቲትዩት ጭምር ማጋለጣቸው ሲታወስ የኢንቬስተሮቹ ተወካይ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ባለፈው ህዳር 2009 በሰጡት ቃለ ምልልስ አጋጣሚ ሆኖ በጋምቤላ እርሻ ኢንስቲትዩት ትግሬዎች እንበዛለን ማለታቸው ይታወሳል።
ለጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወደ 5 ቢሊዮን ብር ወጥቶ መባከኑ የተጋለጠ ሲሆን በመንግስት በኩል የልማት ባንክ ፕሬዝዳንቱን አቶ ኢሳያስ ባህረንና ረዳቶቻቸውን ከማንሳት ውጭ የተወሰደ ርምጃ የለም።
በባንኩ ገንዘብ ይጠየቃሉ ተብለው የሚጠበቁት የጋምቤላ እርሻ ኢንቬስተሮች ተጨማሪ ብድር መጠየቃቸውና ባንኮቹን መወንጀላቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ከጋምቤላ ባሻገር በቤንሻንጉል በእርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች 95 በመቶ ያህሉ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ በደቡብ ኦሞ በተመሳሳይ መስክ ከተሰማሩት ባለሃብቶች የትግራይ ተወላጆች ድርሻ 95 በመቶ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በሶማሌ ክልል ስለተሰማሩት ባለሃብቶች ግን ለጊዜው መረጃ ማግኘት አልተቻለም።