በጃኖራ ቀበሌ የሚካሄደው ውጊያ ቀጥሎአል

ኅዳር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በዳባት ወረዳ በጃኖራ ቀበሌ ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ዛሬ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ ታጋዮች የያዙትን ምሽግ ሰብሮ መግባት ያልቻለው የአገዛዙ ጦር፣ ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ የስነ ልቦና ጫና ለመፍጠር እየሞከረ ነው።

ከጦር ግንባሩ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአካባቢው በብዛት የሰፈሩት ወታደሮች ሞርታርና ዲሽቃ እየተኮሱ አካባቢውን ሲደበድቡ ውለዋል።

የግንባሩን ቃል አቀባይ በቀጥታ ለማግኘት ባንችልም፣ ከአካባቢው ምንጮች እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ዛሬ 5 የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ተገድለዋል።

በአቶ መሳፍንት ተስፉ የሚመራው ተዋጊ ሃይል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ60 በላይ ወታደሮችን መግደሉን እና በርካታ የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን መግለጹ ይታወቃል።

የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ የመሪውን የአቶ መሳፍንትን ሁለት ቤቶች ጨምሮ በጦርነቱ ይሳተፋሉ ያላቸውን አርሶአደሮች ቤት አቃጥሎአል። የእህል ክምራቸውንም እንዲሁ በእሳት አቃጥሎአል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሻለቃ ፈንቴ ወይም በተለምዶ ሙሽሬ እየተባለ የሚጠራው  ነባር ታጋይ በሰሞኑ ውጊያ ተገድሎ ጎንደር ላይ የቀብር ስነ ስርአቱ  መፈጸሙን ምንጮች ገልጸዋል።