በዶ/ር ቴዎድሮስ ሲመራ የነበረው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከግሎባል ፈንድ የተሰጠውን ገንዘብ ከስምምነት ውጪ መጠቀሙና ማጉደሉ ተገለጠ

ግንቦት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጤና ጠበቃ ሚኒስቴርን መርተው ለውጤት እንዳበቁት በመግለጥ ፣ የአለም የጤና ድርጅት መሪ ለመሆን የቅስቅሳ ስራ የጀመሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ኤች አይ ቪ ኤድስንና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመዋጋት በሚል ከግሎባል ፈንድ ለህዝብ የተሰጠውን ገንዘብ ከስምምነት ውጭ ለሌሎች አላማዎች መጠቀማቸውን የሚያመለክት የኦዲት ሪፖርት ቀርቦባችዋል።
ግሎባል ፈንድ በአውሮፓውያን አቆጣጥር በ2010 ፣ 1 ቢሊዮን 3 መቶ ሚሊዮን 35 ሺ 989 ብር ለግሶአል። ጄኔቭ የሚገኘው በምህጻረ ቃሉ GFATM የተባለው የኦዲት ተቁዋም፣ የኢትዮጰያ መንግስት ገንዘቡን ከስምምነት ውጭ እየተጠመበት መሆኑን ጥቆማ ከደረሰው በሁዋላ ባደርገው ማጣራት፣ በ88 ጉዳዮች ላይ ችግሮችን ማግኘቱን በፈንጆች አቆጣጠር ኢፕሪል 19,2012 ባወጣው ሪፖርት አስታውቆአል።
የመጀመሪያው የኦዲት ሪፖርት ከመወጣቱ በፊት ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዲያዩት ከተላከላቸው በሁዋላ ተቃውሞ በማሰማታችው ሪፖርቱ በወቅቱ በተያዘለት ቀን ይፋ እንዳይደረግ ተደርጎአል።
ግሎባል ፈንድ ለጤና ተቁዋማት ግንባታ በሚል 24 ሚሊዮን 196 ሺ 552 ዶላር መድቦ 1 ሺ 309 የጤና ተቁዋማት የተገነቡ ቢሆንም፣ መንግስት ለመድሃኒት መግዢያ የተመደበልትን ገንዘብ ወደ ግንባታ አዙሬዋለሁ በሚል ሪፖርት በማድረጉ 57 ሚሊዮን 851 ሺ 941 ብር በላይ ገንዘብ ከስምምነት ውጭ መጠቀሙንና የድርጅቱ ኦዲተሮችም የጤና ትቁዋማቱን ደረጃ ካዩ በሁዋላ መንግስት ያቀረበውን ምክንያት ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ኦዲተሮች ባደርጉት የመስክ ጉብኝት 165 ሚሊዮን 393 ሺ 27 ዶላር ከወጣባቸው የጤና ተቁዋማት መካከል 71 በመቶ የጤና ትቁዋማት ውሃ የሌላቸው ሲሆን፣ 32 በመቶው ደግሞ ሽንት ቤት የላቸውም። 53 በመቶው ግንባታቸው ከመጠናቀቁ ወለላቸው ተሰነጣጠቁዋል፤ 19 በመቶው ደግሞ ጣራቸው ያፈሳል። 14 በመቶው ብቻ ማይክሮስኮፕ እና የማዋለጃ አልጋዎች ያላቸው ሲሆን፣ 12 በመቶው ብቻ ትክክለኛ የመድሃኒት አቅርቦት አላቸው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሂሳብ ሪፖርቱ 11 ሚሊዮን ዶላር ውጪ ማውጣቱን ቢገልጥም፣ ገንዘቡ ለምን ለምን እንደወጣ ዘርዝሮ ማቅረብ ባለመቻሉ ገንዘቡ እንደተበላ ተቆጥሮ ፣ ኦዲተሮች ገንዘቡ ለግሎባል ፈንድ እንዲመለስለት ጠይቀዋል።
እንዲሁም 7 ሚሊዮን 26 ሺ 929 ዶላር በግልጥ ጎድሎ በመገኘቱ መንግስት ገንዘቡን ለግሎባል ፈንድ እንዲመልስ ኦዲተሮች በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
ሪፖርቱ የአለም ጤና ድርጅት መሪ ለመሆን ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ላሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አደጋን ይዞ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታትሉ ሰዎች ይናገራሉ።