በዶ/ር መረራ ጉዲና የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጠ

ሚያዝያ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ባቀረበላቸው ግብዣ ላይ ተገኝተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ክስ ላይ አቃቤ ሕግ መቃወሚያ አቅርቧል።
ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ምድብ ችሎት ላይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የክስ መቃወሚያ ዝርዝር በችሎቱ ተሰምቷል።
ዶክተር መረራ የቀረበባቸውን ክስ አስመልክቶ ”ክሴ ከእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ጃዋር መሀመድ ጋር አብሮ ሊታይ አይገባም፤ የእኔ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ መንበርነት ከእነሱ ዓላማና አፈጻጸም ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ሊነጠል ይገባል“ ሲሉ ጠይቀዋል። “ቤልጂየም ብራስልስ ለህዝባዊ ስራ ነው የሄድኩት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቁጥር 11/2009 ዓ.ም መሰረት ኮማንድ ፖስቱ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያ አንቀጽ 2/1 ስር የተመለከተውን ተላልፏል የተባለውን እቃወማለሁ“ ብለዋል።
ዶ/ር መረራ “በ2008 እና 2009 ዓ.ም በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ሁከት እና አለመረጋጋት እኔ ልጠየቅ አይገባም። የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ተብሎ በሚጠራው ሚዲያ ላይ ስለ ኢሬቻም ሆነ የሁከት ጥሪ በሚመለከት ቃለ ምልልስ አላደረኩም“ ሲሉ የቀረበባቸው ክስ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው በማለት በክስ መቃወሚያቸው አሰምተዋል።
ዓቃቤ ሕግ የክስ መቃወሚያውን በመቃወም ለችሎቱ ባቀረበበት ወቅት የመሃል ዳኛው በተደጋጋሚ ጊዜ በዶ/ር መረራ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መቅረብ አለመቅረባቸውን ለማረጋገጥ ስማቸውን በመጥራት ለማረጋገጥ ሲሞክሩ ታይተዋል።
አቃቤ ሕግ ባቀረበው መቃወሚያ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተጨማሪ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡