በድርቅ አደጋ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ ተመድ አሳሰበ

ኢሳት (ጥር 1 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ አዲስ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።

የምግብ እና ውሃን እጥረት እንዲሁም የመማሪያ ቦታና የትምህርት ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ መሆኑን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በአፋር፣ ሶማሊ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከወራት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ለነዚሁ ተረጂዎች በተያዘው የፈረንጆች 2017 አም ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 9.2 ሚሊዮን ሰዎች የውሃና የንፅህና ድጋፍን እንደሚሹ ለመረዳት ተችሏል።

በዚሁ የድርቅ አደጋ ከ300 ሺ የሚበልጡ ህጻናት የከፋ የምግብ እጥረት ይደርስባቸዋል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ ህጻናቱን ለመታደግ ልዩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ አስፍሯል።

ከድርቁ በተጨማሪ በጎርፍ አደጋና በግጭቶች ሳቢያ ወደ 350ሺ አካባቢ ነዋሪዎች ከቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉም ድርጅቱ ቢጠቁምም ሊከሰት ይችላል ስላለው የማህበረሰብ ግጭቶች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

ባለፈው አመት በሃገሪቱ በሚገኙ ስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ አጋልጦ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ድርቁ ሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የተለያዩ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ። መንግስት በበኩሉ ድርቁ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

በበርካታ ዞኖች ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲጋለጡ ያደረገው የድርቅ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ የአርብቶአደር የቤት እንስሳትን መግደሉም ተመልክቷል።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁን ለመቋቋም አፋጣኝ ምላሽን ካላደረገ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም ተሰግቷል።