በዳኞች ሹመት የብሔር ተዋጽዖ ጉዳይ አከራከረ

ጥቅምት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጽያ ፓርላማ ዛሬ መደበኛ ስበሰባውን ባካሄደበት ሥነሥርዓት ከዳኞች ሹመት ጋር ተያይዞ የብሔር ተዋጽኦ እና
የብሔር ማንነት ጉዳይ በኢህአዴግ 99 በመቶ የተያዘውን ፓርላማ አከራከረ፡፡

ፓርላማው አቶ ኃለማርያም ደሳለኝ የላኩትን የዳኞች ሹመት  ጉዳይ ላይ በተወያየበት ወቅት አባላቱ ባላተለመደ መልኩ
ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የዳኞቹ የብሔር ተዋጽዖ ምን ያህል የተጠበቀ ነው ከሚል
ጀምሮ ታዳጊዎቹ ክልሎች ማለትም ሶማሌ፣አፋር፣ቤንሻንጉ ለምን አልተካተቱም የሚል ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በአንጻሩ አንድ የም/ቤቱ አባል ከአርጎባ ብሔር እስከዛሬ ከብሔሩ ተሿሚ ዳኛ እንዳልነበርና ተረስቶ የቆየ ጉዳይ መሆኑን
በመጥቀስ በአሁኑ ሹመት ውስጥ አንድ አርጎባ መኖሩ እስየው ነው በማለት ደስታውን መግለጹ ፓርላማውን
አስፈግጓል፡፡

በተጨማሪም አንድ የፓርላማ አባል የአንድን ዕጩ ተሿሚ የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃ መግለጫ ላይ
ብሔር በሚለው ቦታ አማራ ሲደመር ኦሮሞ ተብሎ መጻፉን በመጥቀስ የሴትየዋ ብሔር የትኛው ነው በሚል ያቀረበው
ጥያቄ ብዙዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡

በፓርላማው የተቃዋሚ ፓርቲ ብቸኛ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ዕጩ ዳኛዋ ብሔራቸው አማራ ሲደመር ኦሮሞ መባሉ
ደስታን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡አንድ በአባቱ አማራ ፣በእናቱ ኦሮሞ የሆነ ሰው ቢኖር ተገዶ አንድ ብሔር
ምረጥ የሚባልበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ይህ ዓይነት መብት ሊፈቀድ ይገባል ብለዋል፡፡

ተሿሚ ዳኞቹን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት አምና በብዛት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ተሿሚዎች ይበዙ
ነበር፡፡ዘንድሮ ግን የግል ኮሌጅ ምሩቃን ሁሉ መካተታቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ዳኝነት ትልቅ ሥራ
በመሆኑ ከትምህርት ባሻገር ልምድ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው አንዳንድ ተሿሚዎች ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች መሆኑ
ተገቢ አልነበረም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ፓርላማው ለመጀመሪያ፣ለከፍተኛ እና ለጠቅላይ ፍ/ቤቶች በድምሩ የ45 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡
ፓርላማው በዛሬ ውሎው አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም ለም/ቤቱ ያደረጉትን የመንግስትን
የትኩረት አቅጣጫ የሚያሳየውን ንግግር አስመልክቶ ገዥው ፓርቲ የድጋፍ ሞሸን (የውሳኔ ኃሳብ) አቅርቧል፡፡በሞሽኑ
ላይ ድጋፍ ፣ተቃውሞ፣የማሻሻያ ኀሳብ ተቀብሎ በቀጣዩ ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት
ለማጽደቅ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

የአቶ ሀይለማርያም ካቢኔ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን የአቶ መለስ ዜናዊን ካቢኔ ይዞ ይቀጥል አይቀጥል ገና በውል ባይታወቅም፣ አቶ ጁነዲን ሳዶና ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከሚሰናበቱት ሚኒሰትሮች መካከል እንደሚሆኑ ምልክቶች ታይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለደቡብ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ  ግንባር  ወይም ደኢህዴግ፣ እንዲሁም ምክትሉ ለብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ወይም ብአዴን  በመሰጠቱ ሌላው ቁልፍ የስልጣን ቦታ የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ለህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ( ህወሀት) ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በአዲሱ የስልጣን ድልድል በርካታ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ( ኦህዴድ) አባላት አለመደሰታቸው እየተነገረ ነው።

ህወሀት አብዛኛውን ቁልፍ የሆኑ የመከላከያ፣ የደህንነትና  የፖሊስ ስልጣኖችን በቁጥጥሩ ያስገባ በመሆኑ ምናልባትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታን ለኦህዴድ ፈቅዶ በመተው ያኮረፉ የኦህዴድ አባላትን ለማስደሰት ይጥር ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም ከተለዩ በሁዋላ አቶ በረከት ስምኦን ለአቶ ሀይለማርያምና ለአቶ ደመቀ መኮንን ሹመት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው ይነገራል።