በደንቢያ ወረዳ የብዓዴን አመራሮች እየሸሹ ነው ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 19 ፥ 2008)

በሰሜን ጎንደር ስር በምትገኘው የደንቢያ ወረዳ ለሶስት ቀን ሲካሄድ የቆየውን ከቤት የለመውጣት አድማ ተከትሎ የወረዳዋና የብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች ወረዳውን ለቀም መሸሻቸውን ነዋሪዎች ሃሙስ ለኢሳት አስታወቁ።

በአሁኑ ወቅት ወረዳዋ በነዋሪዎች እየተዳደረች እንደምትገኘ የተናገሩት እማኞች የወረዳው ምክትል አስተዳደርና ሌሎች የብአዴን አመራሮች አካባቢውን ለቀው እንደሸሹ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች በቅርቡ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን በመቃወም የወረዳዋ ነዋሪዎች ከሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የቆየ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።

ነዋሪዎቹ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ረቡዕ ቢጠናቀቅም የተለያዩ ህዝባዊ የተቃውሞ ስልቶች ቀጣይ እንደሚሆኑ አክለው አስረድተዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ተቃውሞ ውስጥ መሆናቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።

የደንብያ ወረዳ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን እያስተዳደሩ እንደሚገኙና በአጎራባች ያሉ ወረዳዎችም ተቃውሞን እያካሄዱ እንደሚገኝ ለደህንነታቸው ስሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ህዝቡ ተቃውሞን እንዲያበቃ ሃሙስ ጥሪ ቢያቀርብም በሰሜን ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም ዞን ስር በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ህዝባዊ ታቃውሞ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።