በደቡብ ክልል በዳውሮ ዞን በዋካ ከተማ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የታሰሩት 20 የሚጠጉ የአገር ሽማግሌዎች መፈታታቸው ታወቀ

ኢሳት ዜና:-ከሳምንት በፊት ከወረዳና ከሌሎች ማህበራዊ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በከተማው የተነሳው ግጭት ያሳሰበው የፌደራሉ መንግስት፣ የታሰሩት የአገር ሽማግሌዎች ተለቀው ችግራቸው እንዲታይላቸው የሚል ትእዛዝ ማስተላለፉ ታውቋል።

በዚህም መሰረት የአገር ሽማግሌዎቹ አርብ ማምሻውን መለቀቃቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ ስርአቱን ሲያወግዙ የነበሩ ወጣቶች ግን በብዛት እየታሰሩ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የአካባቢው ህዝብ ባስነሳው ተቃውሞ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ተዘግተው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ የወካ ከተማ ውጥረት እንዳለ ባለበት ሰአት በቶጫ አካባቢም ውጥረት መኖሩን ለማወቅ ተችሎአል።

የቶጫ አካባቢ ህዝብ ከወረደና ከልማት ጋር በተያያዘ ያቀረበው ጥያቄ እንዳልተመለሰት ለወረዳው ባለስልጣናት በማስታወስ፣ ጥያቄው ቶሎ መልስ የማያገኝ ከሆነ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።