በደቡብ ኦሞ ዞን አራት ህጻናት በጎርፍ ተወሰዱ

ሚያዝያ ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጅንካ አዋሳኝ በሆነው በካይሳ ቀበሌ ቅዳሜ ሚያዚያ 14/2009 ከሰዓት በኋላ ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ አቶ ታደሰ የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ ሁለት ልጆች፣ የታናሽ ወንድማችው አንድ ልጅ፣ እንዲሁም የጎረቤታቸው አንድ ልጅ በአጠቃላይ አራት ህጻናት በጎርፍ መወሰዳቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የጎርፍ አደጋው የደረሰው የዞኑ ግብርና ቢሮ ከቀበሌው ግብርና ጋር በመሆን ከዓመታት በፊት ለአካባቢው አርሶአደሮች የመስኖ ፕሮጀክት በመዘርጋት ሙዝ አምርተው ገቢያቸውን ለማሳደግ በሚል ከፍተኛ የግንባታ ወጪ ተደርጎበት መክኖ ከቀረበው ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በዚህ በተቋረጠው መስኖ ፕሮጀክት ለውኃ ማስተላለፊያ የተቆፈረው የመስኖ ቦይ/ ካናል/ ሳይዘጋ በመቅረቱ በቦዩ የመጣው ከፍተኛ ጎርፍ ከቦዩ ወጥቶ ከቤታቸው አጠገብ ይጫወቱ የነበሩ ህጻናቱን መውሰዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህ የመስኖ ፕሮጀክት ያለበቂ ጥናት ለፕሮፖጋንዳ ሲባል የተሰራ ሆኖ ለአካባቢው አንዳች ጥቅም ሳያመጣ የአገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በከንቱ ፈሶበት የቀረ ከመሆኑም በላይ ፣ ለዚህ ዓይነቱ አደጋ ማኅበረሰቡን አጋልጦኣል ያሉ ነዋሪዎች፣ ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸው ፣ አስተዳደሩ አስፈላጊውን የመከላከያ እርምጃ ከወዲሁ በመውሰድ ህዝቡን መታደግ አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ ዕለት በጣለው ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በቃቆ፣ በነታና ጫሊ ቀበሌዎች የበርካታ ቤቶች ጣሪያ በነፋስ መወሰዱንና ቤቶች ፈራርሰው ነዋሪዎች ያለመጠለያ መቅረታቸውን ፣ ነገር ግን እስከዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 16/09 ዓ.ም ድረስ ለተጎጂ ቤተሰቦች ምንም ድጋፍ አልደረሳቸውም። ከቀበሌው አስተዳደር በቀር ማንም ወደ አካባቢው መጥቶ እንዳልተመለከተ፣ የዞኑ ኤፍኤም ሬዲዮም ስለደረሰው አደጋና ስለሁኔታው ያልዘገበ መሆኑን ተጎጂዎችና ነዋሪዎች በሃዘን ስሜት ገልጸዋል፡፡