በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የምትገኘው የጋፍጋዱድ ከተማ በታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሏ ተገለጸ

ኢሳት (ኅዳር 30 ፥ 2009)

በቅርቡ የኢትዮጵያ ወታደሮችና የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ መጠነ ሰፊ ውጊያ ያካሄዱበትና በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የሚገኘው የጎፍጋዱድ ከተማ በታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሏ ተገለጸ።

በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሚገኙበት የባይደዋ ከተማ በ35 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው በዚህ ስፍራ ባለፈው ወር ውጊያ ተካሄዶ የጎፍ ጋዱድ ከተማ በመንግስት እጅ ገብቶ እንደንበር ሸበሌ ሬዲዮ ዘግቧል።

ይሁና ከቀናት በፊት በአካባቢው ጥቃትን የፈጸሙ አልሸባብ የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት መዲና ከሆነችው ባይዶዋ በቅርብ ርቀት ላይ ያለችውን የጋፍጋዱድ ከተማ ሙሉ ለሙሉ እንደተቆጣጠረ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።

ከተማዋን ለመያዝ በተካሄደው ውጊያ በትንሹ አራት የመንግስት ወታደሮችና ቁጥራቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች መሞታቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተለያዩ የሶማሊያ አካባቢዎች መውጣታቸውን ተከትሎ አልሸባብ ቁልፍ የተባሉ ወታደራዊ ይዞታዎችን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አልጀዚራ ዕማኞችን ዋቢ ባምድረግ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በበኩላቸው ወታደሮቹ ከሶማሊያ እንዲወጡ የተደርገው ለስልታዊ ዕርምጃ እንደሆነና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለሃገሪቱ በቂ ድጋፍ አለማድረጉን በተልዕኮው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውቀዋል።

ታጣቂ ሃይሉ ይዞታዎቹን እያስፋፋ ቢገኝም የኢትዮጵያ ድርጊቱ የሚያሳስብ አይደለም ስትል ትገልጻለች።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማራቻቸው ወደ 4ሺ አካባቢ ወታደሮች በተጨማሪ ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥሩ ያልተገለጸ ወታድርን በተናጠል አሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 ሺ የሚበልጡ የኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ማላዊና ጅቡቲ ሰላም አስከባሪዎች በሶማሊያ በሰላም አስከባሪነት ተሰማርተው ቢገኙም አልሸባብ አሁንም ድረስ የሶማሊያ የጸጥታስጋር ሆኖ ይገኛል።

ይኸው የሰላም አስከባሪ ሃይል ተልዕኮውን አላሳካም የሚል ቅሬታ እየቀረበበት ሲሆን፣ ኬንያና ማላዊ ወታደሮቻቸውን ከሃገሪቱ ለማስወጣት መወሰናቸው ይታወሳል።