በዮናታን ተስፋዬ ላይ የተላለፈው የጥፋተኝነት ብይን “አሳፋሪና በኢትዮጵያ የፍትህ መቀበርን” የሚያሳይ ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞ አቀረበ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2009)

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማክሰኞ በቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ላይ ያስተላለፈውን የጥፋተኝነት ብይን “አሳፋሪና በኢትዮጵያ የፍትህ መቀበርን” የሚያሳይ ዕርምጃ ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞ አቀረበ።

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የሽብርተኛ ወንጀል ህግ በመንግስት ላይ ትችት የሚያቀርቡ ሰዎች የሚደርስባቸውን በደል ማሳያ መሆኑንም በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ባካሄደው የፍርድ ሂደት ተከሳሹ ያቀረባቸውን የክስ ማስረጃዎች ውድቅ በማድረግ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ማስተላለፉ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ይህንኑ ብይን ተከትሎ የብሪታኒያውን ቢቢሲ ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ሃላፊ የሆኑት ሚቼሌ ካጋሪ ዮናታን የሰራው ነገር ቢሆን ሃሳብን በማህበራዊ ድረገጾች መግለጹ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ብይንም በኢትዮጵያ የፍትህ መቀበርን የሚያሳይ አሳፋሪ ድርጊት ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ተከሳሹ ወንጀል ባልሆነው ስራው እስከ 20 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ክስ ጥፋተኛ መባሉ የፍትህ አለመኖሩን በአግባቡ የሚያሳይ ነው ሲሉ ካጋሪ አስታውቀዋል። በኦሮሚይ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ዮናታን ተስፋዬ በማህበራዊ ድረገጾች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የሚዳስሱ ጽሁፎች ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሹ አመፅን በመንግስት ላይ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን አቅርቧል በማለት ባለፈው አመት ግንቦት ወር የሽብርተኛ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ዮናታን ተስፋዬ የቀረበበትን ክስ በመቃወም በርካታ የሰው የመከላከያ ማስረጃ ምስክርነት በማቅረብ ለፍርድ ቤት ሲያስደምጥ ቆይቷል።

የተከሳሹና የአቃቤ ህግን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ፍርድ ቤቱ ግን በመከላከያነት የቀረቡ ማስረጃዎችን ውድቅ በማድረግ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል ብይን ሰጥቷል።

የዮናታን ጠበቃ እንዲሁም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች ብይኑ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ላይ የተላለፈ ነው በማለት ተቃውሞን እየገለጹ ይገኛል።

ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔን ለመስጠት ለቀጣዩ ሳምንት ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።